በጉባ ወረዳ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ የአሶሳ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
በጉባ ወረዳ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ የአሶሳ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች አወገዙ
አሶሳ፤ ሐምሌ 24 / 2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ እንደሚያወግዙ በአሶሳ ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ፡፡
የእምነቱ ተከታዮች የኢድ አል አድሃ /አረፋ/ በዓልን ኮሮናን በመከላከል እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዓሉን እያከበሩ ካሉት የእምነቱ ተከታዮች መካከል አቶ አብዱለጢፍ አልከድር ለኢዜአ እንደተናገሩት የአረፋ በዓልን እያከበሩ ያሉት በደስታ እና በሃዘን ውስጥ ሆነው ነው፡፡
ደስታው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱለጢፍ "ሃዘኑ ደግሞ በክልሉ ጉባ ወረዳ በንጹሃን ላይ የተፈጸመው ግድያ ነው "ብለዋል፡፡
ኮሮናን ለመከላከል በኃይማኖት አባቶች እና በመንግስት የተሰጡ አስተምህሮቶችን እና ህጎችን እያከበርን ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው ይህም እንደከዚህ ቀደሙ ሳይሆን ለበዓሉ የተወሰኑ ሰዎች በመስጊድ በመገኘት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የሰው ህይወት በከንቱ መጥፋት ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ሰሞኑን በጉባ ወረዳ በንጹሃን ላይ ተፈጸመውን ግድያ አውግዘዋል።
"ኮሮና የአረፋ በዓልን ከማክበር አላገደንም "ያሉት ደግሞ ሼህ አላሙዲን አልሃሰን፤ እስልምና ሠላምና ዘረኝነት የሌለበት ሁሉንም የሚያሰባስብ መሆኑን አመልክተው ሰሞኑን በጉባ ወረዳ በንጹሃን ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ እንደሚያወግዙም ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የቦርድ አባል ሃጂ ሙክታር እንድሪስ በበኩላቸው በመስጊድ የሚከበረው የበዓሉ ሂደት በኮሮና ምክንያት የተቀዛቀዘ መሆኑንና ይህም ለህዝብ ደህንነት ሲባል የተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ጤና እና ሠላም ከሌለ ሀገር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ትወድቃለች፤ መንግስት እና ህዝብ በጋራ የሃገር ሠላም ማስጠበቅ አለባቸው " ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ እንደ ኃይማኖት አባት የድርሻቸውን ለመወጣት የእምነቱ ተከታዮችን እያስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከቸልተኝት በመውጣት ራሱን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቅ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ሃጂ ሙክታር በሽታው አልፎ በዓሉን እንደከዚህ ቀደሙ የምናከብርበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አምናለሁ በማለት የተፈጸመው ግድያ አሳዛኝ እና የሚወገዝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ሰሞኑን በተፈጸመ ጥቃት የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በዚህም እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 42 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ይታወሳል።