በአዲስ አበባ የኢድ አል- አድሃ በዓል በታላቁ አንዋር መስጂድ ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የኢድ አል- አድሃ በዓል በታላቁ አንዋር መስጂድ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 24/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ 1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል- አድሃ በዓል በታላቁ አንዋር መስጂድ ዛሬ ተከብሯል።
በዓሉ ፈጣሪን በሚያወድሱ ዜማዎች(ተኪብራ)ና በፀሎት( ሶላት) ተከብሯል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምከር ቤት ፕሬዚዳንት ቤት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ዓመቱ በመልካምነቱ ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን በእኩል የሚያስተናግዱ መሪዎች ማየት የቻልንበት፤ የሙስሊሙ ጥያቄዎች የተመለሱበት መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በአንድነት እየገነቡት ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት የጀመረበት ዓመት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የእምነት ቦታዎችን ያዘጋው የኮቪድ ወረርሽኝ አሳሳቢና አስጨናቂ የሆነበት ዓመት ነው ብለዋል።
ወረርሽኙም ለመከላከል ጥንቃቄውን እንዳያጓድል በተለይም ሙስሊሙ ለፈጣሪ ዱኣ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።
ከእርስ በእርስ መነቋቆር በመውጣት የአገርን አንድነት መጠበቅ፤ ስላምና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ጥሪ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ሱልጣን አማን የኢድ በዓል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ባስጨነቀበት ወቅት ቢሆንም፤ አቅመ ደካሞችን የመርዳት ባህላችን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የእምነቱ ተከታዮች የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፏአቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ በሳዑዲ ዓረቢያ በየዓመቱ የሚካሄደው የሐጅና ዑምራ ተጓዦች ወደ ሥፍራው አልተጓዙም።
ሳዑዲ ዓረቢያ ከውጭ ለሚገቡ ተጓዦችም ቪዛ አልሰጠችም።