ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእስልምና እምነት ተከታዮች የ'እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት' አስተላለፈ

አዲስ አበባ ሐምሌ 23 /2012 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእስልምና እምነት ተከታዮች የ'እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት' አስተላለፈ፡፡

 ሚኒስቴሩ የዘንድሮው ኢድ አል አደሃ በዓል ዋዜማ የሕዳሴ ግድብ ውኃ መያዝ የጀመረበት በመሆኑ ልዩ መሆኑን ገልጾ የ'እንኳን አደረሳችሁ' መልዕክት አስተላልፏል

ሚኒስቴሩ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ድምጻቸውን ከሚያሰሙና በኢትዮጵያና በአረቡ ዓለም ግንኙነት ዙሪያ ምርምር ካደረጉ ግለሰቦች ጋር በመሆን ነው መልዕክቱን ያስተላለፈው።

''የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሁሉም መልኩ ሲታገሉ የቆዩ ኢትዮጵያውያንም ምስጋና ይገባቸዋል'' ብሏል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በአረቡ ዓለም የሚገኙ ወንድሞችን የምትጎዳበት ሳይሆን የምትጠቅምበት ነው።

በተለይ ደግሞ ግብጻውያን የግድቡ ግንባታ እነሱን ለመጉዳት ሳይሆን ልማትን ለማፋጠን የሚደረግ መሆኑን ሊያውቁት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ጥንካሬ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ''የኢትዮጵያ ሕዝብ ማድረግ የፈለገውን ነገር ማድረግና አንገቱን ቀና አድርጎ መሔድ እንደሚችልም ማሳያ ነው'' ብለዋል።

ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያና በአረቡ ዓለም መካከል ያለውን ግንኙነት ሲያጠኑ የቆዩት ፕሮፌሰር አደም ካሚል የዘንድሮ በዓል ለየት ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

''የዘንድሮ በዓል ሁለት መልክ አለው'' ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በጤና በዓሉን ማክበር መቻልና ግድቡ ውኃ ያየዘበት ወቅት መሆኑ የተለየ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አደም ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከበር አስከፊ ከሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በራሱ ተነሳሽነት በአረቡ ዓለም ዘንድ የኢትዮጵያን ከህዳሴ ግድብ የመጠቀም መብት ሲያስተጋባ የቆየው መሓመድ አል አሩሲ በበኩሉ ለሁሉም የእምነቱ ተከታዮች 'እንኳን አደረሳችሁ' ብሏል።

መሓመድ እንደሚለው፤ ሕዝቡ አሁንም አንድነቱን ጠብቆ ወደ ፊትም የሚገጥመውን ትግል ይወጣል።

''በርቱ፣ አገራችንን በምንችለው እንርዳ፣ አብረን እንቁም ከውጭ ያለውን ትግል መመከት የምንችለው በጋራ ስንቆም ነው'' በማለት መልዕክቱን አስተላልፏ።

የዘንድሮው 1 ሺህ 441ኛው ኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በነገው እለት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም