ቀጥታ፡

ድርጅቱ ለአንበጣ መከላከያ የሚውሉ 34 ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23/2012 (ኢዜአ) የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ለአንበጣ መከላከያ የሚውሉ 34 ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በድርጅቱ ቅጥር ግቢ በመገኘት ተቀብለዋል።

በዚሁ ወቅት እንደተገለጸው ድርጅቱ ዛሬ ካስረከባቸው ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ 6 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አድርጓል።

በአጠቃላይም ድርጅቱ 40 ተሽከርካሪዎችን የአንበጣ ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲውል የለገሰ ሲሆን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገባቸውም ታውቋል።

ከተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት ድንኳን፣ አልጋ፣ መቀመጫ፣ ምግብ ማብሰያና ሌሎች ቁሶችንም ነው ፋኦ በዛሬው ዕለት ድጋፍ ያደረገው።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ፋኦ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

ከዚህ በፊትም ድርጅቱ ለኬሚካል ርጭት የሚውል አውሮፕላን ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ ዛሬ በስጦታ የተገኙ መኪኖችም ቶሎ ወደ ቁጥጥር ሥራ እንደሚገቡ አመልክተዋል።

ተሽከርካሪዎቹ የሚውሉት ለአንበጣ ቁጥጥር ሥራ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት ወረርሽኙን ለመካከል በራሱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ድርጅቱ የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር ከኢትዮጵያ ጋር ተናቦ መስራቱ ጉዳቱን ለመቀነስ ያለው አስተጽኦ ትልቅ መሆኑንም አቶ ዑመር አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ድርጅቱ በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ይሄን ድጋፍ በማድረጉም ምስጋና አቅርበዋል።  

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ ፋጡማ ሰኢድ በበኩላቸው "ድርጅቱ ዛሬ የለገሳቸው መኪኖች ለሚደረገው ቅኝትና ቁጥጥር ስራው መሳካት አዎንታዊ ሚና አለው" ብለዋል።   

"የአንበጣ ወረርሽኙን የመከላከሉ ሥራ ፈታኝ ነው'' ያሉት ተወካይዋ፣ በተለይ የግብርና ሚኒስቴር ባለሙያዎች በመስክ ሥራው ላይ ቀንና ማታን የሚያሳልፉ በመሆኑ የተደረገው የቁሳቁስ ደጋፍ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።    

ወደፊትም ፋኦ ድጋፉን በማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት እንደሚዘልቅ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም