የጣና ሃይቅን ከእምቦጭ አደጋ ለማላቀቅ በተፋሰሱ ችግኝ መትከል ይገባል ... የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የጣና ሃይቅን ከእምቦጭ አደጋ ለማላቀቅ በተፋሰሱ ችግኝ መትከል ይገባል ... የምክር ቤት አባላት
ባህርዳር ፤ሃምሌ 23/2012(ኢዜአ) የህዳሴ ግድብ ዋና የውሃ ምንጭ የሆነውን የጣና ሃይቅ ከእምቦጭ አደጋ ለማላቀቅ በዙሪያው ባሉ ተፋሰሶች ችግኝ በመትከል ሁሉም ሊሳተፍ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።
የኢፌዴሪ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በጣና ገዳማት በሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች ትናንት ችግኝ ተክለዋል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደገለጹት የጣና ሃይቅ የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ ሃብት ነው።
ሃይቁ የበርካታ ዘመናት የታሪክ ምንጭ የሆኑ መረጃዎች፣ ቅርሶችና ሌሎች እሴቶች የሚገኙባቸው ገዳማትን አቅፎ የያዘ በመሆኑ አሁን ላይ እንቦጭ አረም አደጋ ተጋርጦበት ማየት ያሳዝናል ብለዋል ።
ጣና ሃይቅ ከሌለ ገዳማቱንና የአባይ ወንዝ የውሃ ፍሰትን ማሰብ የማይቻል በመሆኑ በገዳማቱና በተፋሰሱ አናት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የችግኝ መትከል ስራ አማራጭ የለውም ብለዋል።
እንቦጭን ለመከላከል የችግሩ ምንጭ ምንድን ነው? እንዴትስ ሊፈታ ይችላል? የሚለውና ሌሎች ጉዳዮችን በጥናት በመመለስ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በጣናና አባይ ተፋሰሶች የሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የህዳሴ ግድብን ዘላቂ ውጤታማነትን ማረጋገጥ በመሆኑ በገደማቱ በመገኘት ችግኝ በመትከል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።
በተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው መንግስት የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል።
በያዝነው ክረምትም ሁሉንም ህብረተሰብ በማሳተፍ አምስት ቢሊየን ችግኞችን በመትከል የውሃ ተፋሰስንና የአካባቢውን ስነ ምህዳር ቀድሞ ወደ ነበረበት በመመለስ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል ።
በተለይም በጣና ገዳማትና በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚካሄድ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከጣና አልፎ የህዳሴውን ግድብ በደለል እንዳይሞላና በእምቦጭ እንዳይጠቃ የሚያደርግ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል ።
የኢትዮጵያ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት እንደተረባረቡት ሁሉ ጣናን ከእምቦጭ ለመከላከል በሚያስችሉ ስራዎች ሁሉ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በጣና ገዳማት የችግኝ ተከላ ወቅት የእምቦጭ አረም እያደረሰ ያለውን አደጋን በመገንዘባቸው በቀጣይ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
መንግስት የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክር ቤቱ የተሰጠውን ስልጣን መሰረት በማድረግ በጥብቅ ዲሲፕሊን አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርገም አስታውቀዋል።
በጣና ገዳማት የተተከሉ ችግኞችም የተሻሻለ የማንጎ ዝርያ በመሆኑ ለገዳማቱ ገቢ እገዛ የሚያደርጉና ውበትን የሚጨምሩ በመሆናቸው ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፌደራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጸጋ አራጌ በበኩላቸው በጣና ቂርቆስና ፋሲለደስ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ ችግኝ በመትከል በሃይቁ ላይ የተጋረጠውን የእንቦጭና የደለል አደጋ መከላከል ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል ።
የእምቦጭ መስፋፋት ችግርም በተፋሰሱ ከላይ ጀምሮ የተጠናከረ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ባለመከናወኑ የመጣ እንደሆነ በመግለጽ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል በሃይቁ ዙሪያ በሚገኙ ተፋሰሶች ጠንካራ የችግኝ ተከላ ስራ መከናወን እንዳለበት ገልፀዋል።
መስሪያ ቤታቸው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጣናና አባይ ተፋሰስ አካባቢዎች የጀመረውን ችግኝ የመትከል ስራ አጠናክሮ ለመቀጠልም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በ10 ዓመት ስትራተጅክ እቅድና በብሄራዊ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ፖሊሲ ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት መካሄዱ ይታወሳል።