በግድቡ ዙሪያ የግብጽን የተዛባ አቋም ለዓለም ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት እየሰራን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግድቡ ዙሪያ የግብጽን የተዛባ አቋም ለዓለም ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት እየሰራን ነው
አዲስ አበባ ሐምሌ 23 /2012 (ኢዜአ) ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብጽ የያዘችውን የተዛባ አቋም ለዓለም ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ፍትህ ለሰበዓዊነት የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ስዩም ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በፍትሃዊነት ለመጠቀም እያከናወነች ያለውን ተግባር ሌሎች ተረድተው እንዲደግፉ ለማድረግ በሰሜን አሜሪካና ካናዳ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።
"በሰሜን አሜሪካና በካናዳ በመንቀሳቀስ ስለ ግድቡ ያለውን እውነታ ለማሳወቅና ድምጽችንን ለማሰማት እየሰራን ነው" ብለዋል።
ትክክለኛ የሆነ መረጃ በማቅረብ የአሜሪካ መንግስት ያለውን አቋም እንዲያስተካክል ተጽዕኖ ለመፍጠርም እሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ወደሌሎች የዓለም አገራት የመንቀሳቀስ ዕቅድ እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ አብርሃም፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግድቡ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆሙን በተግባር መግለጽ እንዳለበት ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግስትና አንዳንድ ፖለቲከኞች ከግብጽ ጎን በመሰለፍ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ እያሳዩት ያለው አቋም እንዲስተካከል በትኩረት እንደሚሰሩም ነው ያስታወቁት።
አቶ አብርሃም እንደሚሉት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊን በዓባይ ግድብ ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ ድርጅቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
"ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስከብሩ የማስተባበር፣ የማሰልጠንና የማግባባት ሥራ እንሰራለን" ብለዋል።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቅርበት እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን አንዳስረዱት በግድቡ ዙሪያ ያለውን እውነታ በአሜሪካ ግዛቶች ተንቀሳቅሶ ለህዝቡ ለማሳወቅ ይሰራል።
"የግብጽ ፖለቲከኞች የሚያቀርቡትን የተሳሳተ መረጃ በማሳወቅ የአሜሪካ መንግስት ቢያንስ ገለልተኛ እንዲሆን ጫና ለመፍጠር እንሰራለን" ሲሉም ነው የተናገሩት።
የድርጅቱ ቦርድ አባል አቶ ጌዲዮን ገብረህይወት በበኩላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቻሉት አቅም የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅና ለአሜሪካ እንደራሴዎች ያለውን እውነታ ለማስወቅ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ፍትህ ለሰብዓዊነት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤቱን በአማሬካን ያደረገ ነው።