ቀጥታ፡

በገበያ እጦት ከ65 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ማር በመጋዘን ተከማችቷል

ወልድያ (ኢዜአ) 22/11/2012  በሰሜን ወሎ ዞን ከአርሶ አደሮችና ማህበራት የተሰበሰበው ከ65 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ማር በገበያ መጥፋት ምክንያት በመጋዘን ተከማችቶ እንደሚገኝ የየጁ የማርና የማር ውጤቶች ማጣሪያ ፋብሪካ አስታወቀ። 

የፋብሪካው ሃላፊ አቶ ስዩም ሞገስ እንደገለጹት በሰሜን ወሎ ዞን ስር የሚገኙ ወረዳዎች በነጭና ቀይ ማር ምርታቸው የሚታወቁ ናቸው።

ዞኑ ያለውን የማር እምቅ ሃብት ለመጠቀም የየጁ የማርና የማር ውጤቶች ማጣሪያ ፋብሪካ ተቋቁሞ በ2001 ዓም ወደ ስራ መግባቱን አውስተዋል።

ፋብሪካው በወር በአማካይ 10 ኩንታል ማርና 40 ኩንታል የሠም ምርት ይሸጥ እንደነበር አስታውሰው ከኮሮና መከሰት ወዲህ ግን ገበያው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አስረድተዋል ።

ካለፈው መጋቢት ወዲህ ከአርሶ አደሮችና ከማህበራት የተገዛ 65 ሺህ ኪሎ ግራም ማር በገበያ እጦት በመጋዘን ውስጥ ተከማችቶ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

በመጋዘን ውስጥ ተከማችቶ ከሚገኘው የማር ምርት ውስጥ  35 ሺህ ኪሎ ግራም የተጣራ መሆኑን ጠቁመው ይህን መሸጥ ካልተቻለ ፋብሪካው በመጪው መኸር አዲስ የማር ምርት ለመሰብሰብ እንደሚቸገር ተናግረዋል።

የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ፋብሪካው ያጋጠመውን ችግር ተገንዝበው ገበያ በማፈላለግ እንዲያግዙት ቢጠየቁም አወንታዊ ምላሽ አልተገኘም ብለዋል ።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይሮ በላይነሽ አስናቀ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው ፋብሪካው የገበያ ችግር እንዳጋጠመው የሚገልፅ መረጃ እንዳልነበራቸው በመግለፅ አሁን ግን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል ።

 በፋብሪካው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ኢዮብ መዝሙር በሰጠው አስተያየት ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቀ በፋብሪካው በመቀጠር 3 ሺህ 700 ብር የወር ደመወዝ በማግኘት ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል ።

ኮሮና በፈጠረው የገበያ ችግር ፋብሪካው ለኪሳራ እንዳይዳረግ የተደረገው ጥረት መፍትሄ ባለማግኘቱ ሰራተኞች እንቀነሳለን የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ጠቁሟል ።

የየጁ የማርና የማር ውጤቶች ማጣሪያ ፋብሪካ በ2011 ዓ.ም የክልሉ ህዝብ ሃብት በሆነው በጥረት ኮርፖሬት ባለቤትነት በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ መቋቋሙን የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም