ቀጥታ፡

የግድቡ ግንባታ ለፍፃሜ እስኪበቃ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ በማይጨው ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

ማይጨው ፣ሀምሌ 23/2012(ኢዜአ) የግድቡ ግንባታ ፍፃሜ እስኪገኝ ድረስ ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን አጠናክሮው እንደሚቀጥሉ በትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ለታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል  በትግራይ ክልል የ650 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ መፈጸሙም ተመልክቷል።

ከማይጨው ከተማ ነዋሪዎች መካከል  በንግድ ስራ የተሰማሩት  አቶ መንገሻ ተረፈ እንዳሉት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል  ቦንድ በመግዛት ሲሳተፉ ቆይተዋል።

እስካሁንም የ10ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውና  የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ እስከሚደርስ ድጋፋቸውን አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

 የከተማው ነዋሪ  አቶ ሐጎስ ገብረስላሴ  በበኩላቸው የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውን  ተናግረዋል።

በራሳቸውና ቤተሰባቸው ስም ከ80 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ  ድጋፍ ማድረጋቸውን  አመልክተው ህብረተሰቡ በአንድነት በመሆን ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ እገዛውን መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

''ቦንድ ከመግዛት ባለፈ ቦታው ድረስ በመሄድ ግድቡን መጎብኘት ችያለሁ'' ያሉት አቶ ሐጎስ ለግንባታው የሚያደርጉትን ድጋፍ  እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

"ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር  የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን አለበት "ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ማዕሾ ገብረህይወት ናቸው።

የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መሳካቱን ተከትሎ  ቦንድ ለመግዛት እንዳነሳሳቸውም ገልጸዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በትግራይ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የ650 ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ከክልሉ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ  ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም