ቀጥታ፡

ግድቡ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ታላቅነቷ የሚመለስ ተጨባጭ ማሳያ ነው---የምክር ቤት አባላት

ባህርዳር ፣ሐምሌ 23/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ታላቅነቷ ለመመለስ ለጀመረችው ጉዞ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ግርማ የሽጥላ ለኢዜአ  በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን የቀደመ ታላቅነት ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ አቅሟን ማሳደግ የሚያስችል በቂ የኃይል አቅርቦት ሲኖር  መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ የውሃ ማማ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የዓለም መዳረሻ መሆን እየቻለች በኃይል አቅርቦት ችግር ፋብሪካዎች ጭምር ወደ ማምረት እንዳይገቡ ማነቆ ሆኖ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታትና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማሳካት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።  

የግብፅን ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም የሃገር ውስጥ ባንዳዎችን እኩይ ሴራ በጥበብ በማለፍ የግድቡ የውሃ ሙሌት መከናወኑ ለጥቁር ህዝቦች ኩራትና የኢትዮጵያ ታላቅነተ ለመመለስ ለጀመረችው ጉዞ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን አቶ ግርማ  ተናግረዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል የሚወስንና የሃገሪቱን የመደራደር አቅም የሚያሳድግ በመሆኑ ከፍፃሜ እንዲደርስ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"የአባይ ወንዝ አፈራችንን ለዘመናት ተሸክሞና አራቁቶ በመሄድ ሌሎችን ሲያበለፅግ የኖረ ወንዝ ነው "ያሉት ደግሞ ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ቀለሙ ሙሉነህ ናቸው።  

በኢትዮጵያዊያን  ሃብት እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሀገሪቱን  ከድህነት በማውጣት ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ የሚያሻግረው የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቆ በማየታቸው  የተለየ ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ታላቅ ኢኮኖሚ እየገነባች የመጣች በመሆኑ ጠላቶቿ  ዛሬ የወንዙን መገደብ ብቻ ሳይሆን ነገ በቀጠናው ልትፈጥር የምትችለውን  ተፅዕኖ እንደሚፈሩ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ወይንሸት አስናቀ እንዳሉት ፈጣሪ ዝናቡን እንደጎርፍ አውርዶ ባልታሰበበት ሰዓት የውሃ ሙሌቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል።

የሀገሪቱን መፃኢ ዕድል ለመወሰን ፋና ወጊ የሆነው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በደለል እንዳይሞላ በተፋሰሱ የተጀመረውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ማጠናከርና የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ በማሳደግ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ስትጀምር ለብቻዋ ለመጠቀም  ሳይሆን ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር እኩል ለመገልገል ቁርጠኛ አቋም ይዛ የተነሳች በመሆኑ ድርድሩ በድል ሊቋጭ እንደሚችል እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ወደቀደመ ገናናነቷ የጀመረችውን የዕድገት ጉዞ ለማሳካት ታላቁን የህዳሴ ግድብ በስኬት እንዲጠናቀቅ የምክር ቤት አባላቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም