ቀጥታ፡

የሀገርን ደህንነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በልማቱም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ

ጎባ ሐምሌ 23/2012( ኢዜአ)፡ የሀገርን ደህንነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በልማቱም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገለ ጹ

 በባሌ ዞን ጉራ ዳሞሌ ወረዳ  የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር  የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መትከል መረሃ ግብር አከናውነዋል።

 በመረሃ ግብሩ  ከተሳተፉት የሰራዊቱ  አባላት መካከል ምክትል አስር አለቃ ትዕዛዙ ተጋፋው ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት የሀገርን ሉአላዊነት ከማስከበሩ ጎን ለጎን በአካባቢው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

 ወታደር ጽጌ ደሳለኝ  በበኩሏ  በመንግስት የተሰጣቸውን የሀገርን ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኮ ከመፈጸም በተጓዳኝ  ከአካባቢው ማህበረስብ ጋር በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ላይ በመሳተፍ የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጻለች።

 በመረሃ ግብሩ  የተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪዎችም  በአርብቶ አደር አካባቢ ችግኝ መትከሉ በድርቅ ምክንያት የሚያጋጥመውን ችግር ለመቋቋም ስለሚያግዝ ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ አከባቢ ለማውረስ ያግዛል ብለዋል፡፡

  በመርሃ ግብሩ የተገኙት የጉራ ዳሞሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይ ቦጃ በተለይ አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተፈጥሮ ሀብቱ ጉዳት እንዳይደርስበት የመከላከልና የመጠበቅ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ  ገልፀው ለመከላከያ ሰራዊቱና  ለአከባቢው ነዋሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 በባሌ ዞን በዘንድሮ የክረምት ወቅት ከ165 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ  70 ሚሊዮን መከናወኑንና  ከዚህ ውስጥ  11 ሚሊዮን  ችግኝ በአንድ ጀንበር  የተተከሉ መሆኑን  የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም