መገናኛ ብዙኃን ችግኝን የተመለከተ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ራሳቸውም ተሳታፊ ሆነው መገኘት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ችግኝን የተመለከተ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ራሳቸውም ተሳታፊ ሆነው መገኘት አለባቸው
አዲስ አዲስ (ኢዜአ) ሐምሌ 23/ 2012 የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ችግኝን የተመለከተ መረጃ ለህብረተሠቡ ከማድረስ ባሻገር ራሳቸውም ተሳታፊ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ዛሬ በድል በር አካባቢ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች ባከናወኑት የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ተሳታፊ መሆናቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ተናግረዋል።
የተቋሙ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈራ በቀለ እንደገለጹት፤ የችግኝ ተከላው መካሄድ ከጀመረ ወዲህ የአየር ሁኔታ መሻሻል መኖሩን መታዘብ ይቻላል።
በዚህ ወቅትም በችግኝ ተከላ ዙሪያ ያለው የሰዎች አስተሳሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገርም ችግኝ ተከላ ዜጎች አገራቸውን እንደሚወዱ ከሚያረጋግጡበት መገለጫ መንገዶች ውስጥ አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በዘገባ ህዝቡን ከማነሳሳት ባሻገር ችግኝ በመትከልም ኃላፊነታቸውን ተወጥተው አርዓያ መሆን አለባቸው ብለዋል።
በአመዛኙ አገር በቀል ዛፎች የተከከሉ መሆኑን የተናገሩት ሌላው የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ ናቸው።
በተለይ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አሁንም ክረምቱ ገና በመሆኑ ከሚሰሩት የዘገባ ሥራዎች ጎን ለጎን ችግኝ ቢተክሉ መልካም ነው ይላሉ።
እንደእሳቸው ገለጻ፤ ኢዜአ ባለፈው ዓመት የተከላቸው ችግኞች መጽደቃቸውንና ዘንድሮ ለተተከሉትም እንክብካቤ ይደረጋል።
ሌላ የተቋሙ ባልደረባ የሆኑት ወይዘሪት ሰርካለም ዘለቀ ባለፈው ዓመትም ችግኝ መትከላቸውን አስታውሰው፤ ''ሥራው ትልቅ ደስታ ይሰጣል'' ነው ያሉት።
ችግኞች እያደገና እየዘመነ የመጣው ቴክኖሎጂ የአየር ንብረትን እንዳያዛባ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ክረምቱ ገና እንደመሆኑ መጠን መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ችግኝ በመትከል ተሳታፊ ቢሆኑ እንደ አገር የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።