ቀጥታ፡

ባለሀብቱ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የ5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ ፈጸሙ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ምክንያት በማድረግ የ5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ ፈጸሙ።

ባለሀብቱ ግዥው የተፈጸመበትን ሰነድ ዛሬ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስረክበዋል።

አቶ በላይነህ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ በተለያዩ ጊዜያት የ28 ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያውያን አቅም እየተገነባ የሚገኘው ግድብ የነበሩበት ችግሮች ተፈተው የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚያከውኗቸው ፕሮጀክቶች በኃይል አቅርቦት ረገድ ፋይዳ  እንዳለው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አቶ በላይነህ አረጋግጠዋል።

በግል ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎንም ባለሃብቱ ቦንድ እንዲገዛና ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግ ለማስተባበር እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

መንግሥት በግድቡ ላይ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር እያከናወነ ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ በማድነቅ "ኢትዮጵያውያን  አንድነታችንን በማጠናከር ግንባታውን እናፋጥን" ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የሚከፋፍሉ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና የልማት ሥራዎችን በጋራ በመስራት ከድህነት ለመውጣት እንተባበር ሲሉም ጠይቀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በበኩላቸው አቶ በላይነህ ለግድቡ ቦንድ በመግዛት ባደረጉት አስተዋጽኦ ሁለት ጊዜ የፕላቲኒየም ተሸላሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ የምስጋና ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።

አቶ በላይነህ ቀደም ሲል ባለሃብቶች ቦንድ ግዥ ሲያስተባብሩ መቆየታቸውን ኃላፊው ምሰክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም