ሕዝብን በሙሉ አቅሙ የሚያገለግል አመራር ለማፍራት እየተሰራ ነው -ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝብን በሙሉ አቅሙ የሚያገለግል አመራር ለማፍራት እየተሰራ ነው -ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) ሕዝብን በሙሉ አቅሙ የሚያገለግል አመራር ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ አስታወቁ።
ኃላፊው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ሥልጠና ሲጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ፓርቲው ሕዝብ አገልጋይ አመራር ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ነው።
በከተማዋ የተጀመሩ ዜጋ ተኮር ፕሮጀክቶች ላይ የታየው መልካም አፈጻጸም የለውጡ አመራር ሕዝብን የማገልገል አቅሙን እያጎለበተ መምጣቱን ያሳየበት እንደሆነም ገልጸዋል።
በቀጣይ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የትኩረት አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል።
ከሌብነትና ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት እንደሚሰጥም አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል።
ለዚህም የተለየ ትኩረት የሚሰጥባቸውን ተቋማት መለየታቸው ገልጸዋል።
በለውጡ አመራር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ልምድን ማሳደጋቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።
በከተማ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማስተባበርና በማስፈፀም የአመራሩ አቅም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ሕገ-ወጥነት መቆጣጠርና ዘላቂ ሰላም ማስፈን ቀጣይ ሥራዎች እንደሆኑም አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል።
የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ነዋሪዎች ከአመራሩ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የከተማ ግብርናና የኢንተርፕራይዞች ልማት እንደሚጠናከር አረጋግጠዋል።
በለውጡ ሂደት የታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሁለት ወር ዕቅድ መዘጋጀቱን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ዕቅዱ በዋነኝነት የመልካም አስተዳደር እጦትና በመንግሥታዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማቃለል ያስችላል ብለዋል።
ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ኃላፊው ጠይቀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረትም እንዲያጎለብት አሳስበዋል።
አመራሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በለውጡ ሂደት በተገኙ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ መወያየታቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
በሁለት ዙሮች የሰለጠኑት አመሮች 4 ሺህ 456 መሆናቸው ታውቋል።