ቀጥታ፡

የሲዳማ ህዝብ የብልፅግና ጉዞው እንዲፋጠን በአረንጓዴ ልማት ያሳየው ተሳትፎ የላቀ ነው

ሀዋሳ፤ሐምሌ 22/2012 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ህዝብ በሀገሪቱ የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ እንዲፋጠን በአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ ያሳየው መነሳሳትና ተሳትፎ የላቀ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ ትናንት በክልሉ የተካሄደውን የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ በስኬት መጠናቀቅን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ዘንድሮ በሀገር ደረጃ በአረንጓዴ አሻራ ልማት መረሃ ግብር ለመትከል ከታቀደው 5 ቢሊዮን ችግኝ የሲዳማ ክልል ድርሻን 215 ሚሊዮን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። 

በተለይ በክልሉ በአንድ ጀምበር 6 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ትናንት በተደረገው  ጥረት አንድ ሚሊዮን 600 ሺህ ህዝብ በማንቀሳቀስ ከ11  ሚሊዮን በላይ ችግኝ መትከል መቻሉን አስታውቀዋል።

ህዝቡ ያሳየው ተነሳሽነትና ተሳትፎ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥና የብልፅግና ጉዞ ከዳር እንዲደርስ ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብዙ መሰናክሎችን አልፎ የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት ሲታገልለት የቆየው የክልል ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን  ተከትሎ በፈጠረው ደስታ ተነሳስቶ በተከላው የላቀ ተሳትፎ አሳይቷል ብለዋል። 

በዚህም ህዝቡ ደስታውን የገለጸበትና የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ያለውን ፍላጎት ያሳየበት ነው ብለዋል።  

  በክልሉ ለመትከል ከታቀደው ችግኝ ውስጥ እስካሁን 158 ሚሊዮን የሚበልጠው መተከሉንና   ቀሪ የተከላና የእንክብካቤ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አብርሀም  አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም