ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚያደርጉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው--ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ ድጋፍ የሚያደርጉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ተናገሩ።

የህዳሴው ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ ኢትዮጵያዊያን ለተጨማሪ ሀገራዊ ልማት ቆርጠው እንዲነሱ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዳይሬክተሯ ለኢዜአ እንደገለጹት የግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ "ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደሚችሉ" በተግባር ያሳየ ነው።

በአሁኑ ወቅት ህዝቡ መጀመሪያ የህዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ የነበረውን ተነሳሽነት ይዞ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቅ የቀረውን 26 በመቶ በመሆኑ በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በስፋት እየተሳተፉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህ ንቅናቄ የተፈጠረው በቅርቡ የተደረገው የግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በተግባር በማሳየት መተማመንንና አንድነትን በመፍጠሩ መሆኑንም እንዲሁ።

ሁሉም ዜጋ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሚያደርገውን የጉልበት፣ የገንዘብ፣ የእውቀትና ልዩ ልዩ ድጋፎች አሁን በጀመረው አግባብ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አድርገዋል።

ግድቡን ከመገንባት ጎን ለጎንም የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በመስራትና ችግኝ በመትከል ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የራሳቸውን አሻራ እንዲያሳርፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም