መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉት ዘገባ የራሳቸው ብሔርን ብቻ ያማከለ ሊሆን እንደማይገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉት ዘገባ የራሳቸው ብሔርን ብቻ ያማከለ ሊሆን እንደማይገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ)መገናኛ ብዙኃን አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሚያስተላልፉት ዘገባ የራሳቸው ብሔርን ብቻ ያማከለ ሊሆን እንደማይገባ ተመለከተ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ''የማንነት ፖለቲካና የኢትዮጵያ ሚዲያ'' በሚል የተዘጋጀ ጥናት ቀርቧል።
በጥናቱም ከማንነት ፖለቲካ አንፃር መገናኛ ብዙኃን እያቀረቡት ያለው መረጃ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ተመልክቷል።
ከጥናቱ አቅራቢዎች አንዱ ዶክተር ሙላት ዓለማየሁ እንዳሉት ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት የተደረገው ጥናት አብዛኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ከማንነታቸው ጋር የተያያዙ ዘገባዎች ሲገጥሟቸው እውነታውን ለአድማጮቻቸው ከማሳወቅ ይልቅ ዝምታን ይመርጣሉ።
በዚህም የራሳቸው ብሔር የተነካ ሲመስላቸው ደግሞ ወገንተኛ የመሆን አዝማሚያ ይታይባቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ዋናውን የሚዲያ አጀንዳ በመተው ማደብዘዝና አስፈላጊ ባልሆኑ እሳቤዎች ላይ ማተኮር
እንደሚታይባቸው ምሁሩ አመልክተዋል።
በአሥር የብሮድካስትና የኅትመት መገናኛ ብዙኃን በተደረገው ጥናት ከተካተቱት 133 ዘገባዎች መካከል 109ኙ ከሌሎች መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን በመውሰድ ወገንተኛ መረጃ ለአድማጮቻቸው ወይም ለብሔራቸው ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
'' እኛና እነሱ በሚል እሳቤም ''የራሳቸው ብሔር ያለውን ትክክል በማድረግ በዚህም ማሕበረሰቡ ''ተጎድቻለሁ'' ብሎ እንዲያስብ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዶክተር ሙላት አስረድተዋል።
እንዲሁም እነሱ የሚደግፉት ብሔር ጥፋት ቢያጠፋም አደብዝዘው ዘገባዎችን እንደሚያቀርቡ የጥናቱ ግኝት አመላክቷል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቶች የመገናኛ ብዙኃን አወቃቀራቸው ብሔር ተኮር መሆኑና የሙያውን ሥነምግባር አለመጠበቃቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በመገናኛ ብዙኃኑ የሚቀርቡት ዘገባዎች የራስን ብሔር ደግፎ በማጉላትና የሌላውን ብሔር በማሳነስ አሉታዊ ተጽፅኖ እንደሚያመጣ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል ይላሉ።
የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ዮናስ አሽኔ እንደሚሉት ''መገናኛ ብዙኃን የሚንቀሳቀሱት በአገሪቱ የፖለቲካ ዐውድ መሠረት መሆኑ ይታወቃል።''
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአገሪቱ የሚቀነቀነውን የፖለቲካ ዐውድ ብሔር ተኮር መሆኑ ለመገናኛ ብዙኃንና ለመንግሥት ተቋማት ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የብሔር ወይም የማንነት ፖለቲካ በሁለት መልኮቹ ሊታይ እንደሚገባ ገልጸው፤የመጀመሪያው የአንድ ብሔር አባላት ከሌላው ጋር ያላቸው መስተጋብር ሊታይ ይገባል ብለዋል።
ቀጣዩ ደግሞ የብሔሩ አባላት ከአገረ መንግሥቱ ጋር ያላቸው ግንኙነትን መቃኘት ያስፈልጋል በማለት ምክራቸውን ሰጥተዋል።