በአፈር ማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት የደላሎች ጣልቃ ገብነት በማስቆም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ድኗል-- ኮርፖሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአፈር ማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት የደላሎች ጣልቃ ገብነት በማስቆም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ድኗል-- ኮርፖሬሽኑ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) በአፈር ማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት ወቅት የነበረውን የደላሎች ጣልቃ ገብነት በማስቆም 3 ነጥብ 4 ቢሊዬን ብር ማዳኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ለ2013/14 የምርት ዘመን 18 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት የጨረታ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
ኮርፖሬሽኑ በ2012ና በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት በግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና ሜካናይዜሽን ሥራዎች መሻሻል እየታየ ነው።
በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ (2008-2012) በግብርና ግብዓት አቅርቦትና ሜካናይዜሽን በየዓመቱ በአማካኝ የ14 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ አቅርቦትና ስርጭቱም እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት አቶ ክፍሌ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የ29 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኝ ደላሎችን በማስወጣት ከፋብሪካዎች ተረክቦ መከፋፈል እንደተቻለ አስረድተዋል።
በዚህም በዕቅዱ በተከናወነ የማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መዳኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
አርሶ አደሩ በአምስት ዓመቱ የዕቅድ ዘመን ከአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በአማካኝ 144 ብር ቅናሽ ማግኘቱንና አሰራሩም ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።
መንግሥት የደላሎችን ጣልቃ ገብነት ማስቆም ባይችል ኖሮ፤ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ የአፈር ማዳበሪያ ከዚህ የበለጠ ይጨምር ነበር ብለዋል።
በኢትዮጵያ የ2013/14 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 18 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑ ከግብርና ሚኒስቴር ቀርቦ የጨረታ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ የሚፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ አግኝቶ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።