ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በዓል የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ያለውን በማካፈል እንዲያከብር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋን በዓል የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ያለውን በማካፈል እንዲያከብር ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በመተዛዘንና ያለውን በማካፈል የአረፋ በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ አሳሰቡ፡፡
1 ሺህ 441ኛው የኢዴል አድሃ አረፋ በዓል የፊታችን አርብ ተከብሮ የሚውል መሆኑም ታውቋል።
በዓሉን በማስመልከት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ህዝበ ሙስሊሙ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በመተዛዘንና ያለውን በማካፈል በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብር ጠይቀዋል።
የአረፋን በዓል ልዩ የሚያደርገው ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚበላበት፣ መተዛዘንን፣ አብሮነትንና መረዳዳትን የምናሳይበት የእርድ ስነ ስርአት የሚከወንበት በዓል በመሆኑ ነው ብለዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በርካታ ወገኖች ለችግር የተጋለጡበት ወቅት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ተካፍሎ በመብላት በአሉን ማክበር ተገቢ ነው ብለዋል።
ከሚከናወነው እርድም አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች መስጠት ይገባል ብለዋለ።
የዘንድሮው የአረፋ በዓል እንዳለፈው ኢድ በመራራቅና ራስን ከኮሮና ወረርሽኝ በጠበቀ መልኩ መከበር እንዳለበትም አሳስበዋል።
የዘንድሮ አረፋ በዓል ሀገራችን ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ውሃ ሙሌት ያከናወነችበት ወቅት በመሆኑም ተጨማሪ ደስታ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ልማት ለማስቀጠልም ሰላም ዋነኛው በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም ዘብ በመቆምና በመፀለይ በይቅርታ ወደ ፈጣሪው መመለስ ግድ የሆነበት ወቅት ላይ መደረሱንም አብራርተዋል፡፡
የአረፋ በዓል አደምና ሐዋ የተገናኙበት ሥፍራ እንደሆነ የጠቆሙት ሐጅ ዑመር እድሪስ የአረፋ በዓል ከነብዩላህ ኢብራሂምና ከእስማኤል ጀምሮ ሲከበር የነበረ በዓል መሆኑንም አብራርተዋል።
የዘንደሮው የአረፋ በዓል በሂጅራ አቆጣጠር ለ1 ሺህ 441ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።