ቀጥታ፡

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን-- የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 22/2012(ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ እንዲደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በድሬዳዋ አስተዳደር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናግሩ።

በአስተዳደሩ የአረንጓዴ አሻራን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲካሄድ ተሳታፊ ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል ኮማንደር ገመቹ ካቻ  እንዳሉት ግድቡ ለሳቸውና ለሌላውም የሀገሪቱ ዜጋ ልዩ የታሪክና የማንነት መገለጫ ነው።

መጪው ትውልድ  በራስ መተማመን የተሻለች ሀገር እንዲገነባ መንገድ የተጠረገለት መሆኑን ገልጸው፤ ግድቡን ከፍጻሜ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ በደመወዛቸው ቦንድ ከመግዛት በዘለል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ያስደሰታት መሆኑን የገለጸችው ደግሞ  የመንግስት ሠራተኛዋ ወይዘሪት ዘላለም አዱኛ ናት፡፡

"ለግድቡ መፋጠንና ዳር መድረስ ቦንድ እገዛለሁ፤ ከጓደኞቼ ጋር ተደራጅቼ ገቢ የመሰብሰብ ስራ አከናውናለሁ "ብላለች፡፡

የድሬዳዋ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት መምህር አበበ ታምራት በበኩላቸው መምህራን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ እያሳረፉ ያሉትን ሥራ በህዳሴ ግድቡ ላይ ለመድገም የግድቡ የውሃ ሙሌት መጀመር መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በግሌ ለግድቡ የተዘጋጀውን ቦንድ መግዛት ብቻ ሣይሆን በማህበራዊው ሚዲያ ግድቡ ለሀገር  ምጣኔ ሃብታዊ እድገትና  ለወጣቱ ተጠቃሚነት ያለው ፋይዳ በስፋት እያሳወቅኩኝ እገኛለሁ ብለዋል፡፡

ሌላው የአስተዳደሩ ነዋሪ አቶ በክሪ አሊ ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሃብት በመሆኑ ግንባታውን  በአንድነት ለመጨረስ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

"ከልጆቼ ዳቦ መግዣ ላይ ቦንድ የምገዛው ነገ ለልጆቼ ግድቡ ዳቦ ስለሚያመጣ ነው" ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ እንደተናገሩት፤ የግድቡ የመጀመሪያው ምዕራፍ የውሃ ሙሉቱ በስኬት መጠናቀቅ እሳቸውን ጨምሮ  የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለበለጠ ስኬት አነቃቅቷቸዋል ፡፡

"ከተባበርን የማንፈጽመው ነገር ስለሌለ አንድነታችንን አጠናክረን ለግድቡ ዳር መድረስ ቦንድ በመግዛት ጭምር አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን "ብለዋል፡፡

የአስተዳደሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሣትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው  ጉባኤ የህዝብ መነቃቃት መሰረት በማድረግ 7 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን  በወቅቱ ዘግበናል።፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም