ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በአንድነት መቆም ይገባናል-- የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በአንድነት መቆም ይገባናል-- የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ መከፋፈልና ግጭቶችን በማስወገድ በአንድነት መቆም ይገባናል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።
የውጭ ኃይሎችን ተጽዕኖን መቋቋም እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በማጠናቀቋ ተጽዕኖ ሊያሳርፉባት የሚሞክሩ ወገኖች እንዳሉ ይታወቃል።
አገሪቱ ጫና ውስጥ ባለችበት ወቅት ደግሞ በሕዝቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ለዜጎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ብቻ ሳይሆን፤ ለውጭ ጠላትም ጭምር ክፍተት እንደሚፈጥር አያጠያይቅም።
ይህም በተለይ ጥቅማቸው የተነካባቸው የሚመስላቸውና ግድቡ እንዳይጠናቀቅ የሚፈልጉ አካላትን አጀንዳ ለማሳካት ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር፤ የአገርን ክብርና ሉአላዊነት አሳልፎ መስጠትም ይቆጠራል ይላሉ።
በእንደዚህ ዓይነት የፈተና ወቅት አለመግባባቶችና የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን፤ በአገር ጉዳይ ግን አንድ መሆን እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተባብረው፣ ተሳስበውና ተረዳድተው መኖር ከቻሉ ለሁሉም የሚጠቅምና የሚተርፍ ሃብት ያላት አገር በመሆኗ፤ ሃብቷን በሚገባ መጠቀም እንድትችል አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ትውልዱ ግድቡ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቦቿ የተሰጠ በረከት መሆኑን በመረዳት ግንባታው ለማጠናቀቅ መረባረብ እንጂ፤ ታሪክን የሚያበላሽ መጥፎ አሻራ ጥሎ እንዳያልፍ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አስተሳሰብ ቢኖርም አገራዊ ጉዳይ ላይ አንድ መሆን መተባበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሠላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼኽ መሐመድ ሲራጅ ዑመር በበኩላቸው "ዛሬ በምናበላሸው ነገር ትውልድ ይወቅሰናል አገሪቱ የሁላችንም ናት ለሁላችንም ትበቃናለች " ብለዋል።
“በእድል ያገኙትን በጸባይ ያጡታል “ እንደሚባለው አባባል በተፈጥሮ የታደልነውን ሀብት በፍትሃዊነት እንድንጠቀም መተባበር አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
"ከሁሉም በላይ የውስጥ አንድነት አስፈላጊ ነው ስለ አንድነታችን መስራት ስለ ሰላማችን መስራት የሁላችንም የቤት ስራ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምክትል ፀሐፊ አባ ገብርዔል ወልደሃና ናቸው።
ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን ዐብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሆኑት ፓስተር ሙላቱ ኤርሚያስ በአሁኑ ወቅት የህዳሴው ግድብ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ እንደ መሆኑ መጠን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መረባረብ እንደሚኖርበት ጠቅሰዋል።
ቀደምት አባቶች ክብሯንን ሉአላዊነቷን አስጠብቀውና ያቆይዋትን አገር ወጣቱ ትውልድ በአገሩ ጉዳይ ላይ አንድ ሆኖ በሰላም፣ በአንድነትና በመተባበር ታሪክ ሰሪ ሆኖ ማለፍ ይገባዋል በማለት ተናግረዋል።
የውስጥ ልዩነቶችን በማስወገድም ግድቡ እስከሚጠናቀቅበት እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስም ያለውን ድጋፍና ርብርብ በማጠናከርም የዜግነት ኃላፊነትና ግዴታውን እንዲወጣም የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ74 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁ ይታወሳል።