ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከብሪታንያ የአፍሪካ ሚኒስትር ጀምስ ደድሪጅ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 22/2012(ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከብሪታንያ የአፍሪካ ሚኒስትር ጀምስ ደድሪጅ ጋር በሁለትዮሽ የአገራቱ ግንኙነት መጠናከር እና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙትን የብሪታንያ የአፍሪካ ሚኒስትር ጀምስ ደድሪጅን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ የአገራቱ ግንኙነት እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረጉ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ወረሽኝን በመዋጋት ረገድ ትብብርና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በብሪታኒያ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎቿ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፤ በኢትዮጵያም ወረርሽኙን ለመከላከል በርካታ ጠንካራ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አብራርተዋል።

የአደጋ ጊዜ በጀት ከመመደብ አንስቶ፣ ትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ አብዛኛው የመንግስት ሰራተኞች በቤት ሆነው እንዲሰሩ ከማድረግ አልፎ የ5 ወራትየ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁንም ገለፃ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ ለምታደርገው ጥረት ብሪታኒያ በተለይም የመመርመር አቅምን ለማሳደግ ድጋፍ እንድታደርግ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።

በሁለትዮሽ ትብብርም አገሪቱ እያደረገች ላለችው የልማት ድጋፍ አመስግነው ኢትዮጵያ ከብሪታኒያ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከተፋሰሱ አገራት ግብጽና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እየተደረገ ያለውን ድርድር በተመለከተና ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለአረንጓዴ ልማት እያደረችው ስላለው ጥረትም ገለፃ አድርገዋል።

ቀጠናዊ ጉዳዮችን በተመለከተም ኢትዮጵያ በተለይ ከአጎራባች አገራት ጋር ቀጣናዊ የልማት ትብብሯን አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል።

በሶማሊያ ያለውን የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ያለው የሰላም ሂደት ዘላቂ ለማድረግ ኢትዮጵያ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗንም እንዲሁ።

የብሪታንያ የአፍሪካ ሚኒስትር ጀምስ ደድሪጅ በበኩላቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መምጣቱና እየጠፋ ያለው የዜጎች ህይወት በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ሂደት ላይ የአፍሪካ ህብረት በማደራደር ረገድ የነበረውን ሚና አንሰተዋል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል እውን ስለሆነው ሰላም በሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።

ብሪታኒያ በአውሮፓዊያን አቆጣጠር 1896 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ስትከፍት ኢትዮጵያም በአውሮፓዊያኑ 1923 በለንዴን ኤምባሲዋን መክፈቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሁለቱ አገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በባህል እና የልማት ትብብር ዘርፎች የዳበረ ግንኙነት አላቸው።

ብሪታንያ በልማት ድርጅቷ ዲኤፍ አይ ዲ አማካኝነት እስከ 300 ሚሊዮን ፓውንድ በየዓመቱ ድጋፍ ታደርጋለች።

ኢትዮጵያና ብሪታንያ የ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር (105 ሚሊየን ፓውንድ) የድጋፍ ስምምነት በትላንትናው እለት መፈራረማቸውም  የሚታወስነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም