ቀጥታ፡

የመንግስት ተቋማት ንብረት በማስወገድ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ አደረጉ

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2010- 79 የመንግስት ተቋማት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በሽያጭ መወገድ ያለባቸውን ንብረቶች አስወግደው 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ገቢ ማድረጋቸውን የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ገለጸ፡፡ በሌላ በኩል 99 የሚሆኑ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ደግሞ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ንብረቶችን አስወግደው ማጠናቀቅ አልቻሉም፡፡ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለ178 የመንግስት ተቋማት ከህዳር እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ መወገድ ያለባቸውን ንብረቶች እንዲያስወግዱ ውክልና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም 79 የሚሆኑት መስሪያ ቤቶች ንብረቶቻቸውን በማስወገድ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረግ እንደቻሉ አቶ ይገዙ ተናግረዋል፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ንብረቶቻቸውን በሽያጭና ለሌሎች መስሪያ ቤቶች በስጦታ በማስተላለፍ አበረታች ስራ ማከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡ አምቦ፣ ጎንደር፣ አክሱም፣ ወሎ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ንብረት የማስወገድ ስራውን በአግባቡ ማከናወናቸውን አቶ ይገዙ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ውክልና ከተሰጣቸው ተቋማት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ መስሪያ ቤቶች በተሰጣቸው ስድስት ወር የጊዜ ገደብ ንብረቶቻቸውን አስወግደው ማጠናቀቅ  እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ ክምችት ኖሯቸው ያላስወገዱ መስሪያ ቤቶች መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡ ለንብረት ማስወገድ ስራ ትኩረት ባለመስጠትና የበላይ የስራ ሃላፊዎች ጉዳዩን ባለመከታተል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ምንም አይነት የንብረት ማስወገድ እንቅስቃሴ እንዳልጀመረ የአገልግሎቱ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ተቋማቱ በንብረት አወጋገድ ሂደት የነበራቸው አፈጻጸም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት ከቀረበ በኋላ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጥ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል በአገልግሎቱ በኩል ብቻ መወገድ ያለባቸው ንብረቶች በዘጠኝ ወር ውስጥ ተወግደው 132 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን አቶ ይገዙ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም