በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የ13 ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የ13 ሰዎች ህይወት አለፈ
አሶሳ፤ ሐምሌ 22/2012( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ሽፍቶች ባደረሱት ጥቃት የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
በግድያው የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ ዛሬ እንደገለጹት በክልሉ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አቡቢጃር ቀበሌ የታጠቁ ሽፍቶች ከትናንት በስቲያ በፈጸሙት ጥቃት የ13 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
ከባድ መሳሪያ ጭምር የታጠቁት ሽፍቶቹ የሃገሪቱን ሰላም በማይፈልጉ የውጭና የሃገር ውስጥ አካላት ተልዕኮ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸው የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት ከተጀመረ አንስቶ ስራውንም ማደናቀፍ ዋነኛ ዓላማ አድርገው ወደ አካባቢው እንደገቡም አመልክተዋል፡፡
ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች ህዝቦች መካከል ግጭት መፍጠር ዋነኛ ስትራቴጂአቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
ሽፍቶቹ በተደጋጋሚ በአካባቢውን ለማወክና ጥቃት ለመፈጸም መሞከራቸውን ገልጸው የክልሉ ጸጥታ ሃይል ከመከላከያ ሰራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ተገቢውን እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን ገልጸዋል።
በግድያው የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ያስረዱት ምክትል ሃላፊው፤ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተመራ ቡድንም ወደ ስፍራው ገብቶ አካባቢውን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አመልክተው የክልሉ ጸጥታ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡