አመራሩ የፀረ ሰላም ሃርሎች አፍራሽ ተልዕኮ ለማምከን መስራት አለበት ...የደቡብ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች

ዲላ ሐምሌ 22/2012 (ኢዜአ) በየደረጃው የሚገኘው አመራር አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸውን አካላት በመለየት አጀንዳቸውን ማምከን እንዳለበት የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አሳሰቡ።

የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የከፍተኛ አመራር ኮንፍራንስ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ አቋም በመያዝ ተጠናቅቋል ።

በመድረኩ ላያ የተገኙት የደቡብ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ሄለን ደበሌ እንዳሉት ባለፉት አመታት በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የተመዘገበው እድገት ከጥራትም ሆነ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንፃር ችግር ስለነበረበት ለውጥ አስፈልጓል።

ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ሁለት አመታት ለህዝቡ ትልቅ ተስፋ የሰጠና ውጤት የተመዘገበበት ስራ  ቢከናወንም  በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን በማግዘፍና ስኬቶችን በማቅለል ለውጡን ለማጣጣል የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ገልጸዋል ።

ለዚህ ደግሞ አመራሩ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይ በደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥያቄን ሽፋን በማድረግ የራሳቸውን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ሲባል ክልሉን የስጋት ቀጠና ከማድረግ ባለፈ አመራሩንና ህዝቡን ከተግባር ስራ እንዲነጠል ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የታገለበት ዋና አላማ የህዝብ ነጻነትንና እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን ተከትሎ በክልሉ በየደረጃው የታፈኑ የህዝብ ጥያቄዎች በአደባባይ መነሳታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ የሚያገኝ ሆኖ ሲያበቃ በተሳሳተ መንገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በዚህ ላይ አመራሩ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በመፍጠር አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸውን አካላት በመለየት አጀንዳቸውን ማምከን እንዳለበት አሳስበዋል።

ለህዝቦች የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀውን ለውጥ በማስቀጠሉ ረገድ አመራሩ ግንባር ቀደም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ  ሌላው የፓርቲው ከፍተኛ አመራርና የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ ናቸው።

ህዝቦች በነጻነት ለሚያነሱት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ የሚሰጥ ፓርቲና መንግስት መኖሩ እየታወቀ የተለያዩ አጀንዳዎችን በማንሳት የዞኑን ሰላም ለማወክ የሚደረጉ ጥረቶችን ተከታትሎ ማምከን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከመከላከል ጎን ለጎን የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጌዴኦ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፀሃይ ወራሳ በበኩላቸው ኮንፍራንሱ አመራሩ የተግባርና የአመለካከት አንድነት በመያዝ ለውጡን የሚገዳደሩ አካላትን በጋራ ለመመከት አቋም የተያዘበት ነው።

ለውጡን ተከትሎ በሀገር ደረጃ የተመዘገቡ ውጤቶችን ወደ ታችኛው ህብረተሰብ እንዲደርስ የዞኑ አመራር ልማትን በማረጋገጥ ለውጡ ስር እንዲሰድ መስራት እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ኮንፍራሱ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መክሮ ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል የጋራ አቋም በመያዝ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም