ቀጥታ፡

የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ የወጣቱ ርብርብ አስፈላጊ ነው..የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር

ሐምሌ 22/2012 (ኢዜአ) የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ የወጣቱ ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ አሳሰቡ ።

በኦሮሚያ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት ሲካሄድ የነበረው የ14 ቀናት ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት የማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ትናንት ማታ በሸራተን አዲስ ተካሔዷል ።

በትንሿ ኢትዮጵያ በተመሰለውና ላለፉት 14 ቀናት በተካሔደው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ከኦሮሚያ ክልል ካሉት ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ 120 ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል ።

በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ባስተላለፉት መልእክት ይኸን እድል አግኝታችሁ በልዩነቷ የምታምረውን ኢትዮጵያን በማየታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልእክት ለወጣቶቹ አስተላልፈዋል ።

የሀገራችን የወደፊቱ የብልጽግና ጉዞ ስኬት በወጣቶች ሰላማዊ ትጋት ይመሰረታል ያሉት ወይዘሮ ፊልሰን የኢትዮጵያ የወደፊት የተስፋ ጉዞ ካለወጣቱ ርብርብ እውን አይሆንም ብለዋል።

አገሪቷ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ህብረተሰቡን በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ ለተሳተፋችሁ ወጣቶች በክልሉ ስም ትልቅ ምስጋና ይገባችኋል ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የከተማ ክላስተር አስተባባሪዋ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ናቸው።

ወጣትነት ሁሉ ነገር ነው ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ ከማፍረስ መገንባትን መርጣችሁ አገር ለማሻገር ያደረጋችሁት ገንቢ ተሳትፎ ለሌሎች ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለአመራሮችም ጭምር ተምሳሌት ናችሁ ብለዋል።

የዜግነት አገልግሎት ማንም ሰው ዜጋ በመሆኑ ብቻ ለህብረተሰቡ የሚከፍለው ትንሹ ዋጋ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙና አህመድ ናቸው።

በዚህ የበጎ ፈቃድ አገለግሎት የተከላችሁት ችግኝ ብቻ ሳይሆን ፍቅር ነው ያሉት ወይዘሮ ሙና የለገሳችሁ ደም ደግሞ የወገን ህይወት ከመታደግ ባሻገር የህዳሴውን ግድብ በገንዘብ ከመደገፍ አልፎ በደማችን ጭምር እንጠብቃለን የሚል መልእክት በግልፅ የሚያሰተላልፍ ነው ብለዋል ።

የየክልላቸውን  ወጣቶች ወክለው በዚህ በጎ ስራ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች እንዳሉት አንዳቸው የሌላውን ወግና ባህል ያሳወቃቸውና የኢትዮጵያን አንድነት በተግባር ያዩበት ጉዞ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአዲሱ የሲዳማ ክልል የመጣችው ወጣት ቤተልሔም አሰፋ በሰጠችው አስተያየት በጉልበት፣ በገንዘብና በአስተሳሰብ በሚገለጸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያየንበት ስእል ነው ብላለች።

ከእንጂባራ ከተማ ጀምሮ የህዳሴን ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት የተመለከተው ወሰን ተሻጋሪው የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አባላት በአዳማ፣ አዋሽ፣ ሀረር፣ ጅጅጋና ጅማ ከተሞች ላይ ችግኝ ተክለዋል፣

የኮቪድ መከላከል ግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ፣ ደም በመለገስና የአረጋዊያን መኖሪያ ቤቶች በመጠገንም ገንቢ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ።

በጉዞቸው ማጠናቀቂያም  በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የትውልድ መንደር በሻሻ አንደኛ ደረጃ ትምህረት ቤት ላይ ተጨማሪ ክፍሎችን ሰርተዋል።

በዚህ በጎ ተግባር ለተሳተፉትና ድጋፍ ላደረጉት አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም