ለግድቡ ግንባታ ዳር መድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የምክር ቤት አባላትና አመራሮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለግድቡ ግንባታ ዳር መድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የምክር ቤት አባላትና አመራሮች ገለጹ
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 22/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት አባላትና አመራሮች ተናገሩ።
ምክር ቤቱ ባደረገው ዓመታዊ ጉባኤ በተያዘው የበጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ የሚውል 7 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የቀረበውን ዕቅድ አጽድቋል፡፡
በጉባኤው የተሳተፉት የምክር ቤቱ አባል ዶክተር ኢንጂነር ወርቁ ኮሼ እንደተናገሩት የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቁ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ያኮራና ብሔራዊ አንድነትን ያደመቀ ሥራ ነው፡፡
ግድቡ ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና ሌላውም ዘርፍ ወደ ብልጽግና እንድትጓዝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
"በሙያዬ፣ በገንዘቤ፣ በሚጠበቅብኝ ማንኛውንም ጉዳይ ድጋፌን አጠናክራለሁ፤ የታቀደው 7 ሚሊዮን ብር እንዲሳካ ኃላፊነቴን እወጣለሁ " ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የግድቡ ሙሌት የድሬዳዋ ነዋሪን ያስደሰተና ለቀጣይ ድጋፍ መነቃቃት መፍጠሩን የገለፁት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ሰላህዲን አብዱልረሂም ናቸው፡፡
በተለይ ግድቡ እንደተሸጠ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ሀገር ለማተራመስና የህዝብ ተሣትፎ ለማዳከም የተደረገው ጥረት ሁሉ ባዶ መቅረቱ ድርብ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"አሁን በሁሉም ዘንድ መነቃቃት ተፈጥሯል፤ የታቀደውን ገቢ መሰብሰብ እንችላለን" ብለዋል፡፡
አቶ ኤሊያ ተሾመ በበኩላቸው ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ነዋሪ የአካባቢውን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ ተቀናጅቶ የመጠበቅና ከኮሮና ራሱንና ቤተሰቡን የመከላከል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት እንዲሳካ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ ሠራተኛው፣ የንግድ ማህበረሰብ፣ ባለሃብቱ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል በቦንድ ግዥና በስጦታ 90 ሚሊዮን ብር ለግንባታው ማበርከታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በተያዘው የበጀት ዓመትም ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ለመደገፍ ዕቅድ መያዙን ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ወደ ብልጽግና የሚያሻግርን ግድብ ከማጠናቀቅ የሚያግደን ምንም ኃይል የለም ብለዋል።
ህዝቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ዓመታዊ ዕቅድ ላይ ትናንት ተወያይተው የ7 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ የተቀመጠውን ዕቅድ አጽድቀዋል፡፡