ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ የ192 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ የ192 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ
አዲስ አበባ ሀምሌ 21/2012 (ኢዜአ)የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖን ለመከላከል የሚያግዝና ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።
የኢትዮጵያ መንግስት ከፊንላልድ መንግስት ጋር በመተባበር ሥራ ላይ የሚውለው ፕሮጀክት በማህበረሰብ አቀፍ የተፋጠነ የውሃና ንህጽና ፕሮጀክት (ኮዋሽ) አማካይነት ለ6 ወራት የሚተገበር መሆኑ ታውቋል።
ለፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ መንግስት 81 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ፤ የፊንላንድ መንግስት 2 ነጥብ 67 ሚሊዮን ዮሮ ወይም 111 ነጥብ 17 ሚሊዮን ብር መድበዋል።
ፕሮጀክቱ በአማራ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኑ 76 ወረዳዎች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚተገበር ይሆናል ተብሏል።
በዚህም በገጠር ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበረሰብ አቀፍ የተፋጠነ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና የንህጽና አገልግሎት ተደራሽ እንደሚደረጉ ነው የኮዋሽ ኮሙኒኬሽን አማካሪ አቶ መላኩ ተኮላ የተናገሩት።
ለእዚህም ኮዋሽ ከክልሎቹ ጋር በመሆን በስድስት ወራት ውስጥ በወረዳዎቹ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የዝግጁነት፣ ምላሽና አቅም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚያከናውን አመልክተዋል።
አቶ መላኩ እንዳሉት በወረዳዎቹ የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና የወረርሽኑን ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ የመከላከያ ግብዓቶችን ከማቅረብ ባለፈ በለይቶ ማቆያዎች ውሃ የማቅረብ ሥራዎች ይሰራሉ።
በትምህርት ቤቶች በጤና ተቋማት መጻዳጃ ቤቶችን መስራትና የማዳስ ስራም በፕሮጀክቶቹ መካተታቸውን ነው የጠቆሙት።
የውሃ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ከዚህ በፊት በውሃና በንህጽና ላይ ማህበረሰቡን በማስተባበር ውጤታማ ሥራ መስራቱን ጠቁመዋል።
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚያስችሉ አንዱ እጅ መታጠብ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን አገራዊ ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ዶክተር በሻህ እንዳሉት ኮሚሽኑ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በአዲስ አበባ በጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎችና ለይቶ ማቆያ ቦታዎች በትላልቅ ሮቶዎች ውሃ እያቀረብ ይገኛል።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችና የንጽህና መጠበቂያዎችን ሲያቀርብ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ በክልሎችም የቫይረሱን ወረርሽን ለመከላከል ተጋላጭነታቸው የጎላ በሆኑ አካባቢዎች በ13 ሚሊዮን ብር የውሃ መሳቢያ ፓምፕ፣ የሮቶ፣ እና የንህጽና ቁሶችን ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።
የኮዋሽ ፕሮጀክት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት እ.አ.አ ከ2011 እስከ 2020 የኢትዮጵያ መንግስት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር እና የፊንላንድ መንግስት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ በ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የገጠር ማህበረሰብን ተጠቃሚ ማድረጉ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።