ቀጥታ፡

አማራ ክልል ኮሮናን በመከላከል ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ ይሰራል .. የክልሉ ርእሰ መስተዳድር

ባህርዳር፤ ሐምሌ21/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከልና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የህዝቡን የልማት ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ። 

ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ተመስርተው የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና የማጠቃለያ ሃሳብ ሰጥተዋል።

በክልሉ በዚህ ዓመት የተጀመረው ሰላም የማስፈን ስራ መልሶ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በቀጣዩ ዓመትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ ይስተዋሉ የነበሩ የሰላም ችግሮች አጀንዳ በሚያስይዙ ኃይሎች በውስጣችን የሚፈፀም በመሆኑ የውስጣችንን ችግሮች ለማረምና ለማስተካከል ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።

የሀገሪቱ ስርጭቱ እየሰፋ የመጣው የኮሮና ቫይረስ የህዝቡ የመኖር ስጋት እንዳይሆንና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ችግሮችን በማረም በመከላከል ስራው ርብርብ እንደሚደረግ አስረድተዋል ።

ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥና የኮሮና  ወረርሽኝን በመከላከል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት እንደሚከናወኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

ለዚህ ደግሞ ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ቀጣይ ትኩረት የተሰጣቸው አቅጣጫዎች መሆናቸውን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

የገቢ አቅምን ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴም የንግዱ ማህበረሰብ በሚያገኘው ገቢ ልክ ግብር እንዲከፍል የምክር ቤት አባላት ግንባር ቀደም ሆነው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል ።

ባሳለፍነው በጀት ዓመት በክልሉ ከተሞች በዓለም ባንክ በተመደበ 600 ሚሊዮን ብር የመንገድና ሌሎች የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች በአጥጋቢ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የዓለም ባንክ ለቀጣይ አመት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደቡ የከተሞችን ዕድገት ሊያፋጥኑ በሚችሉ ስራዎች ላይ እንዲውል ይደረጋል ነው ያሉት።

በርካታ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ወደክልሉ እየመጡ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ዕድገት ሊያረጋግጡና ስራ አጥነትን ሊቀርፉ የሚችሉትን ቅድሚያ በመስጠት ይሰራል ብለዋል።

ግብርናውን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም የምርጥ ዘርና የመካናይዜሽን አቅርቦት አሁንም ያልተፈቱ ፈተናዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦትን በክልሉ አቅም ለመፍታትም ለአማራ ምርጥ ዘር ድርጅት የዘር ማባዣ በቂ መሬት በመሰጠቱ በቀጣይ ችግሩ እንደሚቀረፍ ጠቅሰዋል።

የምክር ቤቱ አባልና የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የፀጥታና የፖለቲካ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር በመሆን ባከናወነው ስራ የተሻለ የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረግ ተችሏል።

ክልሉን ለማተራመስ ተልዕኮ ተሰጥቶአቸው በረቀቀ ሁኔታ ሲንቀሳቀሰሱ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉንም አብራርተዋል።

የክልሉን ሰላምና ደህንነት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስጠበቅ ሁላችንም ልዩነት ሳይኖረን ተግባብተንና ተደማምጠን በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

 የክልሉ 5ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን በማፅድቅ ማምሻውን ይጠናቃቀል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም