ቀጥታ፡

ለ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ዓይነስውራን ተማሪዎች የኦንላይን ፈተና ስልጠና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ  ሀምሌ 21/2012 (ኢዜአ) ከአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ለተውጣጡ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ተፈታኝ አይነስውራን ተማሪዎች በኦንላይን ፈተና እንዲወስዱ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሃሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን በዘንድሮ አመት የ12ኛ ክፍል ፈተናን የሚወስዱ ሁሉም ዓይነስውራን ይወስዱታል ተበሎ ታምኗል።

ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የሆኑ 400 ዓይነስውራን ተማሪዎች እንዳሉ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከእነዚህ መካከል 250 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በኦንላይን ለመውሰድ የሚያስችል ስልጠና ለመከታተል በአዲስ በአበባ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ስልጠናው በተጀመረበት ወቅት እንዳሉት የትምህርት ዘርፉ በቴክኖሎጂ ታግዞ በሚከወንበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ ነው።

ይህንንም ሁኔታ ለማሻሻል ሚኒስቴሩ የትምህርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየሰራ መሆኑን ተናግረው የተማሪዎችና መምህራንን ምዘና በኦንላይን መስጠትም የዚሁ አካል መሆኑን አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን በኦንላይን ለመስጠት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የሆኑ ዓይነስውራን ተማሪዎች ፈተናውን ራሳቸውን ችለው መፈተን እንዲችሉም ስልጠናው ተጀምሯል።

ለተማሪዎቹ መሰረታዊ የኮምፒውተር ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ይህም ፈተናውን በራሳቸው እንዲፈተኑ ያስችላቸዋል ተብሏል።

በአገሪቱ ያሉ ከ3 ሺህ በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በኮምፒውተር ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ይህ እውን ሆኖ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ሲስፋፋ ዓይነስውራን ተማሪዎች በአካባቢያቸው ሆነው መሰል ስልጠና ያገኛሉም ብለዋል።

ዓይነስውራን በትምህርት ግብአቶች እጥረት ምክንያት ተፅዕኖ ሲደርስባቸው መቆየቱን የገለፁት ደግሞ  የተስማሚ ቴክኖሎጂ ማዕከል ለአይነስውራን ዳይሬክተር ዶክተር ታምሩ እውነቱ ናቸው።

በትምህርት ገበታና በስራ ላይ ዓይነስውራን እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀው ማዕከሉ ላለፉት 20 አመታት በርካቶችን ለትምህርት የሚረዱ የብሬል መፅሀፍትንና በቴክኖሎጂ የታዘገ ስልጠና እየሰጠ ሲደግፍ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የዛሬው ስልጠናው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ተማሪዎች ለኦንላይን ፈተናው ዝግጁ እንደሚያደርግም አብራርተዋል።

በስልጠናው ተሳታፊ የሆኑ ተማሪዎችም ከዚህ ቀደም ከኮምፒውተር ጋር የተያያዘ እውቀታቸው የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው አሁን የሚያገኙት ስልጠና ያለ ድጋፍ በራሳችን እንዲንሰራ ያግዘናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ይስሙ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ዓይነስውራን መልቀቂያ ፈተናዎችን በሰዎች በመታገዝ መፈተናቸው በንባብና በማጥቆር ስህተት የለፉበትን ያህል እንዳያገኙ ያደርጋቸው ነበር ብለዋል።

ዓይነስውራን ተማሪዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲፈተኑ ሊደረግ መሆኑ ይህንን ችግር የሚፈታ እንደሆነ በመግለፅ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ዩኒቨርሲቲው በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት በተቋረጠበት ወቅት በኦንላይን ሲያስተምር መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዓይነስውራን ተማሪዎች ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን ገልፀው ኮሮና ቫይረስን ተከትሎ ኦንላይን ትምህርት በሚሰጥበት ወቅትም ዓይነስውራን ተሳታፊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ስልጠናውን ለመከታተል እስካሁን በቦታው ያልተገኙ ዓይነስውራን ተማሪዎች በቀጣዮቹ ቀናት ስልጠናው በሚሰጥበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (5 ኪሎ ካምፓስ) እንዲገኙ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ እንደተገለፀው ከዛሬ 14 አመት በፊት በተጠና የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ ዓይነስውራን ይገኛሉ።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም