ቀጥታ፡

ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ የ12 ሚለዮን ብር ቦንድ ገዛ

አዲስ አበባ ሐምሌ 21 /2012 (ኢዜአ)ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን በማስመልከት ለግድቡ ግንባታ የ12 ሚለዮን ብር የቦንድ ግዥ ፈጸመ።

ኩባንያው ከዚህ ቀደም በስድስት ዙር የ51 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ የፈጸመ ሲሆን ግድቡ ውሃ መያዝ መጀመሩን ምክንያት በማድረግም በዛሬው ዕለት የ12 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዢ ፈጽሟል።

የቦንድ ግዥ የተፈጸመበትን ሰነድ ዛሬ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስረክቧል።

የኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ ኩባንያው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።   

''ግድቡ ተጠናቆ ኢትዮጵያዊያኖች የግድቡ በላቤትነታችንን እስክናረጋግጥ ድረስም ድጋፋችን ይቀጥላል" ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው፣ "የሕዳሴው ግድብ በውሃ ሲሞላ  የኢትዮጵያዊያን ልብም በተስፋ ተሞልቷል" ብለዋል።

ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፣ ግድቡ ተጠናቆ ለአገር ኢኮኖሚ በሚኖረው አስተዋጽኦ ተቋሙም ተጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ፍቅርተ ታምር፣ የሕዳሴው ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ተሳትፎ እያደረገ ላለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይ ለግድቡ ግንባታ እዚህ ደረጃ መድረስ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የሕዳሴው ግድብ ከዳር እንዲደርስ አሁን ያለውን መነሳሳት በመጠቀም ህዝቡ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ርብርባቸውን እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የሕዳሴው ግድብ በመጀመሪያው ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የያዘ ሲሆን የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ 70 ቢሊዮን ሜትሪክዩብ ውሃ እንደሚይዝ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም