ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎቹን አስመረቀ

ደብረ ብርሀን (ኢዜአ) ሐምሌ 21/2012 የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በ2ኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 61 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ።
የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ አንዳርጌ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት በትምህርት ዘርፉ ላይ በርካታ እንቅፋቶች አጋጥመዋል።
የመማር ማስተማሩ እንዲቋረጥ በመደረጉም ተማሪዎችን አቅም በፈቀደ መንገድ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተለይም የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቴክኖሎጂ እንዲከታተሉ በማድረግ ለዛሬው የምረቃ ቀን ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።
ዩኒቨርስቲው ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎችም በቀን፣ በማታና በሳምንታዊ የትምህርት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ተከታትለው ማጠናቀቅ የቻሉ ናቸው ብለዋል።
ተመራቂዎቹ በጤና፣ በግብርናና ተፈጥሮ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ቀመርና የቢዝነስ የትምህርት መስክን ጨምሮ በ21 የትምህርት ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው ተብሏል።
ዩኒቨርስቲው ለ12ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከልም 52ቱ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ ሀገሪቱ የተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች ውስጥ መሆኗን አመልክተው፤ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር ፈጥና እንድትወጣ በቆይታቸው ወቅት ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዶክተር ደረጀ አሳስበዋል።
በአካውንቲንግና ፋይናስ የትምህርት ዘርፍ 3 ነጥብ 91 በማምጣት የተመረቁት አቶ ገብረሀና ደበበ በበሰጡት አስተያየት በተመረቁበት ዘርፍ ህዝባቸውንና አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ ናቸው ።
በእናቶችና ህፃናት ጤና የተመረቁት ወይዘሮ ዘነቡ አጎናፍር በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል ።
ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት በኮሮና ቨይረስ ምክንያት ተወካይ ተማሪዎችና የዩኒቨርስቲው የሴኔት አባላት ብቻ ተገኝተው መረሐ ግብሩን ተከታትለዋል።