ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ባለሃብቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ባለሃብቶች ገለጹ
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሃብቶች ገለጹ።
የዋሪት ሙሉጥላ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ትህትና ሙሉሸዋ እንደገለጹት፣ የግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን የትብብራቸውን ውጤት ማየት የጀመሩበት ነው።
ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን በማስታወስ ከወራት በፊት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብ እኛነታችንን የሚያስተባብረን አንድ የሚያደርገን ፕሮጄክት በመሆኑ፣ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያውያን ከተባበሩና ለጋራ ዓላማ በአንድነት ከቆሙ ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ግድቡ ትክክለኛ ምሳሌ መሆኑንም ገልጸዋል።
“እንደ ባለሃብት የሥራችንን ፍሬ ማካፈል ካለብን አገራችን ለምትሰራቸው ግዙፍ ፕሮጄክቶች ነው ” የሚል እሳቤ አለን ብለዋል።
በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ግድቡ በትክክለኛው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ በመሆኑ፣ በቀጣይም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የተናገሩት ደግሞ የባኖ ትሬዲንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉአለም ማህተመ ናቸው።
ከወር በፊት የግማሽ ሚሊዮን ብር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ከድህነት ለመውጣት ለምታከናውነው ማንኛውም ፕሮጄክት በአንድነት መተባበር ያለብን ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ ህብረተሰቡ የግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ቢጠናቀቅም ቀሪ ሥራዎችን ለማፋጠን ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ባለሃብቱን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ግንባታውን ከዳር ለማድረስ ጽህፈት ቤቱ በቀጣይ በሚያዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር አሻራውን እንዲያሳርፍ ጠይቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የህዳሴ ግድብ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ74 በመቶ በላይ መድረሱን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።