ቀጥታ፡

በህግ ማስከበር ሂደት መንግስት በአግባቡ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል-የሕግ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ሐምሌ 21/ 2012 (ኢዜአ)መንግሥት የምርመራና የክስ ሂደቶችን በፍጥነት በመከወን ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥምረት ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የህግ ባለሙያው አቶ መሱድ ገበየሁ፤ የሕግ የበላይነት ሲባል መንግሥት ራሱ ህግን ሲያከብር፣ የዜጎችን ደህንነት ሲጠብቅና ህግ የሚጥሱ አካላትን ተጠያቂ ሲያደርግ እንደነበር ይገልጻሉ።

በአገራዊ ለውጡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የህግ ማሻሻያዎችና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ተከናውነው መሰረታዊ ለውጦች ታይተዋል።

በአንፃሩ ደግሞ የመንጋ ፍርድ፣ ግድያና ንብረት ማውደም የተስተዋለበት አጋጣሚ እንደሆነም ይናገራሉ።

 የመንግስት ዋና ሚና የዜጎችን ደህንነት ማስከበር ነው ያሉት አቶ መሱድ፣ ሰላምን በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ የደህንነት ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶችና ሌች የጸጥታ ተቋማት ትልቁን ሚና የሚጫወቱ ቢሆንም ትልቅ ክፍተት የሚታይባቸውና መንግስትን የሚያስተቹ ናቸው ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አዲሱ ጌታነህ በበኩላቸው የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው አሳታፊነት ካለው የሕግ አወጣጥና ገለልተኝነት ባለው የሕግ አፈጻጽም ሂደት ነው።

ከዚህ በፊት መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ያስር እንደነበርና በሕግ ጥላ ስር የነበሩ ሰዎችን ደግሞ ህጉን ባልጠበቀ መልኩ የተለያዩ ነገሮች ይደረስሱባቸው ነበር ብለዋል፡፡   

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዜጎችን መብት ሲጥሱ ነበሩት ከመንግስት በተጨማሪ ሌሎች አካላትም መኖራቸውን አቶ አዲሱ አስረድተው እንዚህ አካላት በተለያ የአገሪቱ አካባቢዎች ንብረቶችን ከማውደም አልፈው የዜጎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የመንግሥት ህግን የማስክበር አቅም መላላትና የጎራ መደበላለቅ፣ በወቅቱ መተግበር የነበረባቸው ስራዎች በጊዜው ባለመደረጋቸውና የህግ የበላይነት አለመከበሩ ለአሁናዊ ጥፋቶች መንስኤ እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግስት የዜጎችን ህልውና መታደግ፣ አጥፊዎችንም በሕግ ተጠያቂ ማድርግ አለበት ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ የሕግ ማስከብር ተግባራት ቀደም ሲል ህዝቡ ሲጠይቃቸው የነበሩ መሆናቸውን አስታውስው፤ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የወንጀል ተጠጥርጣሪዎች ላይ የተጀመሩ የምርመራና የክስ ሂደቶች በፍጥነት ተጠናቀው ጥፋት ፈጻሚዎች እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

ሰዎችን መክሰስ ብቻ ዋስትና የለውም ያሉት ባለሞያዎቹ ቀደም ሲል የተፈጸሙ የወንጀል ተግባራትም ፍትህ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ከባለ ስልጣን ጀምሮ ሁሉም ዜጋ ጥፋት ሰርቶ እስከተገኘ ድረስ ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ  በህግ ጥላ ስር  መጠየቅ እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

አገርን ለማፍረስ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ፣ ዜጎች እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየወደመ የመንግስት ከልክ ያለፈ ሆደ-ሰፊነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አብራርተዋል።

የዴሞክራሲ ምህዳር ማስፋትና ሆደ ሰፊነትም ፅንሰ ሃሳብም ከሕግ የበላይነት ጋር እንደማይገናኝ ይገልጻሉ።

ከመንግስት በተጨማሪ ዜጎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች የየራሳቸው ድርሻና ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

በወንጀል ተግባራት የተሳተፉት ሁሉ እንደ ግለሰብ እንጂ በብሄርም ሆነ በሌላ ስም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ እንደማይገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም