ሰብዓዊነት የሚሰማውና ስለ ሰው ልጅ ክብር የሚቆረቆር ትውልድ ለመፍጠር በስነ-ምግባር የማነጽ ስራ ያስፈልጋል -- የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሰብዓዊነት የሚሰማውና ስለ ሰው ልጅ ክብር የሚቆረቆር ትውልድ ለመፍጠር በስነ-ምግባር የማነጽ ስራ ያስፈልጋል -- የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 20/2012 ( ኢዜአ) ትውልዱ ሰብዓዊነት የሚሰማውና ስለ ሰው ልጆች ክብር የሚቆረቆር እንዲሆን ከመሰረቱ በስነ-ምግባር የማነጽ ስራ መሰራት እንደሚገባ የሐይማኖት አባቶች አሳሰቡ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ግጭት፣ አለመግባባትና ሁከት ለንጹሃን ዜጎች ሕልፈት እንዲሁም ለበርካታ የአገርና የሕዝብ ንብረት ውድመት ምክንያት እየሆኑ ነው።
የእነዚህ የጥፋት ተግባራት መደጋገምም የተለመደ ሆኖ መታየት መጀመርም ትውልዱ ላይ ያለመስራት ውጤት መሆኑን ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት አባቶች የገለጹት።
የሰው ልጅ በእውቀቱ፣ በዝናው፣ በችሎታው በሃብቱና በንብረቱ ሳይሆን በሰውነቱ ብቻ ክብር ይገባዋል የሚሉት አባቶቹ ፈጣሪ የፈጠረውን ፍጡር ሰው ጉልበተኛ ሆኖ በግልፍተኝነትና በስሜታዊነት ለማጥፋትና ለመበደል መጣርም የሃጥያትና የክፋት መበራከት ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።
ልጆችን ከሕፃንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ስለ ሰው ልጅ ክቡርነት የሚረዱና ሰብዓዊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ በመልካም ስነ-ምግባር ቀርጾ በማሳደግ ረገድ በእምነት ተቋማትም በመንግስትም በኩል አልተሰራም ብለዋል።
በመሆኑም አስነዋሪና ከሰብዓዊነትም ከሐይማኖትም ከኢትዮጵያዊነትም የራቁና የተወገዙ ተግባራት ርህራሄ በጎደለው መልኩ ሲፈፀሙ ለመታየቱ ምክንያት እንደሆነም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያዊያን አማኞች ናቸው ተብሎ ቢታመንም የሚስተዋሉት ተግባራት የአባቶች አስተምህሮ መሳቱን፣ እምነትም መተዉን ያሳያሉ ነው ያሉት።
የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ እንጦንስ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ የሰው ህይወት ማጥፋትና ሌሎች ሰብዓዊነት የጎደላቸው ተግባራት የኢትዮጵያውያን ስርዓትና ባህል ያለመሆኑንና ማስተዋል የጎደለበትና በስሜታዊነት በመነሳሳት የሰው ህይወት የጠፋበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የሠላምና እርቅ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት ሼኽ መሀመድ ሲራጅ ኡመር እንደገለጹት አንዱ የአንዱን ህይወት መቅጠፍ የቀደሙ አባቶችን ትምህርት መሳት ሀይማኖትን መከተል መተው ማለት ነው።
ሀይማኖት ማለት እዝነት መሆኑን ገልጸው ፤ 90 ከመቶ በላይ አማኝ ባለበት አገር እንደዚህ አይነት ድርጊት መፈጸም ማለት እምነትን መተው ማለት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምክትል ጸሃፊ አባ ገብርዔል ወልደሃና የሰው ልጅ የወንድምና የእህቶቹ ህይወት ጠበቃ መሆን እንደሚገባው ገልጸው ፤ ከዚሀ በተቃራኒ ግን የሰው ህይወትን ማጥፋት ፈጣሪን ያለማወቅና ያለመቀበል ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
የሰው ልጅ ሀይማኖቱን ባህሉን መለስ ብሎ ማሰብ ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜያት በአገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ለብዙ አመታት ትውልድን የማነጽ ስራዎች በመንግስትና በሀይማኖት ተቋማት ያለመሰራታቸው ወጤት ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያንና አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሆኑት ፓስተር ሙላቱ ኤርሚያስ ናቸው።
በቀጣይም ትውልድን በስነ ምግባር የማነጽ ስራዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የትኛውም ሃይማኖት ቢሆን ጥላቻና መገዳደልን ሳይሆን ሕዝቦች በአንድ ላይ ሆነው ያለ ልዩነት ተዋደውና ተከባብረው እንዲኖሩ ያዛል፤ ያስተምራልም ብለዋል አባቶቹ።
የተበላሸና የተሳሳተ ታሪክ ካለም ያንን ላለመድገምና ለማስተካከል መጣር፣ ለትውልዱም መልካም ነገር ማውረስ እንጂ ስህተትና ጥፋትን ደጋፊም ደጋሚም መሆን አይገባም ሲሉም መክረዋል።
ትውልዱ የሕዝቦችን አንድነት የሚሸረሽሩና ለሠላም ጠንቅ የሆኑትን እንዳይከተልም ከስር ከመሰረቱ በስነ-ምግባር የማነጽና ኮትኩቶ የማሳደግ ስራ መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ለዚህም በተለይ የግብረ-ገብነት ትምህርት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ መሰጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የጥላቻ፣ የመገዳደል፣ የመጠፋፋትና መሰል ተግባራት የተወገዙና ታሪክ በማበላሸት መጥፎ አሻራ ጥለው የሚያልፉ በመሆናቸው ሕዝቦች ይህን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።
ለትውልዱ በጎ በጎውን በማስተማር፣ ሰብዓዊነት የሚሰማውና ለአገርና ለሕዝቡ ተቆርቋሪ በማድረግ ቤተሰብ፣ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና መንግስት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።