ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የሲዳማ ክልል አመራሮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የሲዳማ ክልል አመራሮች ገለጹ
ሀዋሳ ሐምሌ 20/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል አመራሮች ገለጹ።
ከአመራሮቹ መካከል በክልሉ የሸባዲኖ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ዶዮ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በለውጡ ማግስት መንግስት በወሰደው ቆራጥ አቋም ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የግድቡ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌቱ በስኬት መጠናቀቁ እንደ አድዋ ድል የሚቆጠር ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ ለግንባታው ሲደርጉ የነበረው ድጋፍ እስከፍጻሜው ድረስ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ በየዓመቱ በወር ደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍልጶስ ናሆም ናቸው።
"ግድቡ የሁሉም ኢትዮጰያዊያን የጋራ ሃብታችን ነው" ያሉት አቶ ፊልጶስ ግድቡ በመሀል ያጋጠመውን ፈተና አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ በመድረሱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጽ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው፤ ከውስጥና ከውጭ የተለያዩ አካላት ግድቡ እንዳይሳካ የተለያዩ ሳንካዎች እየፈጠሩ ባለበት ወቅት የሙሌቱ ዜና መሰማቱ ጥንካሬያችንን ለዓለም ያሳየንበትና ጠላት ያፈረበት ነው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ለታለመለት ዓለማ እስከሚውል ድረስ ቦንድ በመግዛትና በ8100 ከመሳተፍ ባለፈ በሴከተር መሥሪያ ቤቱ ያሉ ሠራተኞች ተሳትፎአቸውን ለማጠናከር እንደሚያስተባብሩ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት መሳካቱ ግድቡ ተሸጧል በማለት ያልተገባ ወሬ ለማናፈስ የሞከሩ ግለሰቦች ሴራቸው ከንቱ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
መሰረተቢስ ወሬ አንድነታችንን ለመሸርሸር የሚደረግ በመሆኑ ይህንን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።
ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ክልሉ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮች በማዘጋጀት ድጋፉን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የግድቡ ውሃ ሙሌቱ መጀመር የፈጠረው ደስታ ያቀዱትን የልማት ግቦች ለማሳካት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝቡ ለጠላትና ከፋፋይ አስተሳሰብ ጆሮ ባለመስጠት አንድነቱን የሚያጠናክሩ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሲዳማ አካባቢ ህዝብ ቀደም ሲልም ከ400 ሚሊዮን የማያንስ ብር ለግድቡ ግንባታ አስተዋፅኦ ማድረጉንም አቶ ደስታ አስታውሰዋል።