ቀጥታ፡

የኮሮና ቫይረስ እስኪጠፋ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን -ባለሃብቶች

መቀሌ፣ ሀምሌ 20/2012  (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሆቴሎቻቸውን ለለይቶ ማቆያ የሰጡ የመቀሌ ከተማ ባለሃብቶች ቫይረሱን እስኪጠፋ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

በመቀሌ የሚገኙ የሆቴል ባለቤቶች ከኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብረ ሀይል ጋር ዛሬ ውይይት አካሔደዋል ።

ባለ ሆቴሎቹ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ እስኪጠፋ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ገልፀዋል ።

የደስታ ኢንተርናሽናል ሆቴል ስራ አስክያጅ አቶ ሙሉ ሓዱሽ  እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በለይቶ ማቆያ አሰራር ወደ ሆቴሉ ለሚመጡት ሰዎች ስልጠና በወሰዱ ሰራተኞች አማካኝነት ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ከክልሉ ውጭ የሚመጡትን  እንግዶች በቆይታቸው ጥንቃቄ በተሞላበት መስተንግዶ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

የዓምድና ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረእግዚአብሄር መኮንን በበኩላቸው የለይቶ ማቆያ ጊዜአቸውን ለማሳለፍ ወደ ሆቴላቸው የሚመጡ እንግዶች አስፈላጊውን የመገልገያ ዕቃዎችና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዲደርሳቸው ይደረጋል ።

በሆቴሉ ለሚገኙ ሰራተኞች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ስልጠናዎች ቢሰጣቸው አገልግሎቱ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገው ገልፀዋል ።

ከኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብረ ሀይል ጋር በተቀናጀ መንገድ መስራታቸው ዜግነታዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ የኢትዮ መኝታ ቤት ባለቤት አቶ ገብረህይወት ተክላይ ናቸው።

አልፎ አልፎ የሚያጋጥማቸው የጸረ ተህዋስያን ኬሚካልና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እጥረት እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል።

 በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩት ባለሃብቶች የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል መንግስት በሚያደርገው ጥረት በአጋርነት መቆማቸው ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ያሉት ደግሞ የቴክኒክ  ግብረ  ኃይል አስተባባሪና  የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሐጎስ ጎዲፋይ ናቸው።

ባለፉት አራት ወራት በክልሉ የሚገኙት ሆቴሎችና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በለይቶ ማቆያነት በማገልገል ከ37 ሺህ በላይ ሰዎች ተቀብለው በማስተናገድ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል ።

የሆቴል ባለቤቶችና ሰራተኞች  የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረጉት ያለውን  ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ንኡስ ግብረሃይል አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ቸርነት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም