"የሕዳሴው ግድብና የዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በኢትዮጵያዊያን አብሮነት ላይ የተመሰረተ ነው" - ዶክተር ይልማ ስለሺ - ኢዜአ አማርኛ
"የሕዳሴው ግድብና የዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በኢትዮጵያዊያን አብሮነት ላይ የተመሰረተ ነው" - ዶክተር ይልማ ስለሺ
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ሊሰናከል የሚችለው አብሮነታችንን ማስቀጠል ካልቻልን ብቻ ነው ሲሉ የሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪና የውሃ መሃንዲሱ ዶክተር ይልማ ስለሺ ተናገሩ።
አሁን እየታዩ ያሉ የኢትዮጵያ ስኬቶች አገሪቷ ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ እየገባች እንደሆነ ያሳያሉም ነው ያሉት።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ መሃንዲስ ዶክተር ይልማ ስለሺ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ እየገባች መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ አብሮነትን፣ ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና በራስ መተማመንን ያመጣ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ግድቡን በራሳቸው አቅም ከመገንባት፣ በድርድሩ ሂደትም በማንም ላይ ተስፋ ሳያደርጉ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳት ከስኬት ላይ መድረሳቸው ለቀጣይ ጉዞ ጥንካሬ የሚሰጥ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተማረ የሰው ኃይል፣ ምቹ የአየር ንብረት፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት ገልፀው እየመጣ ያለውን አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ለማሳካት የሚቀራት 'ሠላምና አንድነት ነው' ብለዋል።
ይህንን ካሳካች ታላላቅ ኢንቬስተሮች አጋጣሚውን ለመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ጊዜ ቅርብ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴው ግድብ ያላትን አቋም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅና የመጠቀም መብቷን በማስከበር ያደረገችው ጥረት ትልቅ ንቅናቄን መፍጠሩንም አክለዋል።
ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም ማጠናቀቅ መቻሏ ብቻ በዓለም አቀፍ ተሰሚነቷ ላይ ጉልህ ሚና እንዳለውም ነው የጠቀሱት።
ይህ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን አፍሪካዊያን እርስ በእሳቸውና ከሌላው ዓለም ጋር የሚኖራቸውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠነከር እንደሆነም ዶክተር ይልማ አብራርተዋል።
እየመጣ ያለው የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድገትና አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ እንዲሳካ ኢትዮጵያዊያን ሰሠላማቸውንና አንድነታቸውን ጠብቀው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ያካሄደችው ድርድር የሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ይልማ ከፍተኛ ጥንካሬን የሚጠይቀው በዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ላይ የሚደረገው ድርድር እንደሆነም ጠቁመዋል።
የዓባይ የውሃ አጠቃቀምም ይሁን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በኢትዮጵያዊያን አንድነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንምም አስገንዝበዋል።
ዶክተር ይልማ እንደገለጹት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ ኃይሎች ይህን ዕድል ለማሰናከል የሚሞክሩት ኢትዮጵያዊያንን በማለያየት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ አንድነቱን ሊጠብቅ ይገባል።