የህዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት የህዝቡን ድጋፍ ዳግም አነቃቅቶታል - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ የውኃ ሙሌት የህዝቡን ድጋፍ ዳግም አነቃቅቶታል
መቱ ሐምሌ 19 /2012 መንግስት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከነበሩበት ችግሮች በማላቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውሀ ሙሌት ማብቃቱ ህዝቡ ለግድቡ ያለው የድጋፍ ስሜት መልሶ እንዲያንሰራራ ማድረጉን የመቱ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሰራተኞች ገለፁ::
የዩኒቨርሲቲው መምህራኑና ሰራተኞች ለኢዜአ እንደገለፁት የግድቡ ግንባታ ከሁለት አመታት በፊት በነበረው አመራር በሚፈለገው መንገድ ባለመከናወኑ የህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲቀዘቅዝ አድርጎት ነበር ።
በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ፋኩሊቲ መምህር አቶ ስለሺ ዱባለ እንዳሉት መንግስት ባለፉት ሁለት አመታት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራትና በግድቡ ግንባታ ሂደት የነበሩ ችግሮች በመፍታት ለዚህ ደረጃ ማብቃቱ የሚያስመሰግነው ነው::
"የግድቡ ግንባታ እንደተጀመረ ሀብታም ደሀ ሳይል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በስጦታና በቦንድ ግዢ ይረባረብ እንደነበር ጠቅሰው በወቅቱ የነበረው መንግስት ብልሹ አሰራር የግንባታ ሂደቱን በማጓተቱ ድጋፉን እንዲቀዛቀዝ ማድረጉን ተናግረዋል ።
አሁን የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌቱ መጠናቀቁ እንደ አዲስ የህዝብ ተስፋ በመጫሩ የግድቡን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ መነቃቃት መፍጠሩን ገልፀዋል ።
መንግስት በሁለት አመታት ውስጥ ያሉበትን የድርድር ጫናዎች ተቋቁሞ እና ግድቡ በብልሹ አሰራር የገጠሙትን ችግሮች በመፍታት ለውሀ ሙሌት ማድረሱ በህዝቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ እንዳሳደገ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ተኮር ሬድዮ ጣቢያ ስራ አስከያጅ አቶ አስረሳኸኝ ሀይለመስቀል ናቸው::
የግብፅ ባለስልጣናት የድርድር ሂደቱን ወደ አሜሪካና የተባበሩት መንግስታት ለመውሰድ ቢሞክሩም ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት እንዲካሄድ ኢትዮጵያ የሰራችው የዲፕሎማሲ ስራ ትልቅ ድል ነውም" ብለዋል::
የግድቡ ግንባታ ውጤት በመታየቱ ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማበርከት ያነሳሳዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል ።
በዩኒቨርስቲው የውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የውጭ ግንኙነትና ትብብር ቡድን መሪ አቶ ሐብታሙ ወንድሙ በበኩላቸው ከውጭ ሀይሎች ጋር በመሆን የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚጥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች አገራቸውንና ወገናቸውን እየጎዱ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል ።
በግድቡ ስም የሀገር ገንዘብ ያጠፉና ለመሸጥ ያሰቡ ኃይሎች ተመልሰው "ግድቡ ተሽጧል" በማለት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መንዛታቸው የውኃ ሙሌቱ እርቃናቸውን እንዳስቀራቸው ተናግረዋል ።
የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሌት የፈጠረውን ደስታ ተከትሎ እስከ ፍፃሜው ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን ለመቀጠል መነቃቃት ፈጥሮልናል ብለዋል ።
ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ተሳትፎአቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል::