በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለሕዳሴ ግድብ የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለሕዳሴ ግድብ የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 19/2012 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጉለሌ ከፍለ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ።
በራስ አቅምና ወጪ እየተገነ ለሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያስፈገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ በተለያዩ መንገድ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሚልኮ አህመድ ለግድቡ ግንባታ የህዝቡ ተሳትፎ ተቀዛቅዞ እንደነበርና ይህም የተፈጠረው ከግድቡ የግንባታ ሂደት ጋር በተያያዘ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት በክፍለ ከተማው ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ ዕቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና ህዝባዊ ተሳትፎ የተቀዛቀዘ በመሆኑ ዕቅዱ ዳግም ለመከለስና 2 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ወይዘሮ ሚልኮ ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ሊሰበሰብ መቻሉን ገልጸዋ።
ወይዘሮ ሚልኮ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ተሳትፎ መነቃቃት እየታየበት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንቦት 15 ቀን 2012 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫን ከሶማሌ ክልል መረከቡ የሚታወስ ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ዋንጫው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እንዲዘዋወር በማድረግ ለግድቡ ግንባታ ገቢ የማሰባሰብ ተግባር እያከናወነ ይገኛል።
እንደ ወይዘሮ ሚልኮ ገለጻ፣ በየክፍለ ከተሞቹ እየዞረ ያለውን ዋንጫ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ይረከባል።
በክፍለ ከተማው የሕዳሴ ግድቡ ዋንጫ የ10 ቀናት ቆይታ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
በዋንጫው 20 ሚሊዮን ብር የማሳባሰብ ዕቅድ መኖሩንና ይሄንንም ገቢ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ማሳካት ስለማይቻል ከወዲሁ ገቢ የማሰባሰብ ሥራው መጀመሩን ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስም ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ለማሰባሰብ መቻሉን ነው ወይዘሮ ሚልኮ የጠቆሙት።
በሕዳሴው ግድብ የታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ ንቅናቄ መጀመሩንና ለዚህም ህዝባዊ ተሳትፎን መሰረት ያደረገ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ዋንጫውን ምክንያት በማድረግ ለሚሰበሰበው ገንዘብ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውና የሚያደርጉትንም ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ላለፉት አራት ቀናት በነበረው የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ስብስባ የክፍለ ከተማው አመራሮች ለሕዳሴው ግድብ የ200 ሺህ ብር ቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማው አመራሮችና ሠራተኞች ለሕዳሴ ግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በሕዳሴ ግድብ ዋንጫው ከ500 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎችን በማሳተፍ በሚደረገው ቅስቀሳ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ከአዲስ አበባ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በ2012 በጀት አመት በአገር አቀፍ ደረጃ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ860 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምከር ቤት ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከአገር ውስጥና ከውጭ ዳያስፖራ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት መሰብሰቡ ታውቋል።