ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለመትከል ከታቀደው ችግኝ 80 በመቶ ተተክሏል

አዲስ አበባ  (ኢዜአ) ሀምሌ 19/2012 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ በዘንድሮ የክረምት ወቅት ለመትከል ከታቀደው ችግኝ እስካሁን 80 በመቶ ያህሉ መተከሉ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ዛሬ ማለዳ ድል በር በሚገኘው የእንጦጦ የደን ክልል ሁለት ሺህ ችግኝ ተክለዋል።

የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የፓርቲው አመራሮች ላለፉት አራት ቀናት ሲያደርጉት የነበረውን ስብሰባ መጠናቀቅ አስመልክቶና ለድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ለማኖር በማለም እንደሆነ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ''ስብሰባው በወቅታዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች፣ የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና በክረምቱ ለመስራት የታሰቡ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነበር'' ብለዋል።

በክረምቱ ለመስራት ከታቀዱ ስራዎች መካከል በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ለመትከል የታቀደውን 5 ሚሊዮን ችግኝ ውጤታማ እንዲሆን ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ለመትከል ከታቀደው አምስት ሚሊዮን ችግኝ እስካሁን አራት ሚሊዮን ወይም የዕቅዱ 80 በመቶ መተከሉን አመልክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ የተከላ መርሃ ግብርና አጠቃላይ በአረንጓዴ ልማት የሚሰሩ ስራዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም የተጋረጠባትን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና መፍትሔ ለማበጀት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ስራ ዘላቂነት ያለው ተግባር እንደሆነ ነው አቶ ተስፋዬ ያስረዱት።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በአረንጓዴ አሻራ 800 ሺህ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ወደ 500 ሺህ ገደማ መተከሉን ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጋራ ርብርብ እያደረገ መሆኑንና የታቀደውን ከግብ በማድረስ ከቀጣዩ ወር አጋማሽ በኋላ ወደ እንክብካቤ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጉለሌ ከፍለ ከተማ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሚልኮ አህመድ እንዳሉት፤ በክፍለ ከተማው ባለው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሴት አመራሮች ጠንካራ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

የጉለሌ ከፍለ ከተማ የተፋሰስና የአረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አማረ አብጤ በክፍለ ከተማው ባለድርሻ አካላትን አሳታፊ ያደረገ የእንክብካቤ ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

''ባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በክፍለ ከተማው 469 ሺህ ችግኝ መተከሉንና ከዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው ችግኝ ጸድቋል'' ብለዋል የጽህፈት ቤት ኃላፊው።

በክፍለ ከተማው ከአረንጓዴ ልማት ስራዎች ተጨማሪ ዜጎች በየቤታቸው የጓሮ አትክልት በመትከል በከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት በመላው ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም