ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው በምርምር የተረጋገጡ 5 የባህል መድኃኒቶች ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው በምርምር የተረጋገጡ 5 የባህል መድኃኒቶች ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18/2012 ( ኢዜአ) ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው በምርምር የተረጋገጡ አምስት የባህል መድኃኒቶች ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ደግሞ መንግሥት ዘርፉ ካለው እምቅ አቅም አንጻር ትኩረት አልሰጠውም በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በኢንስቲትዩቱ የባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ተካ ለኢዜአ እንደገለጹት መድኃኒቶቹ ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ እሴት ተጨምሮባቸው ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል።
መድኃኒቱ ለሰው የቆዳ በሽታዎች እንዲሁም ለእንስሳት ሕክምና እንደሚውሉ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ዜጎች የተጠቀሙባቸውና አሁንም ጥቅም የሚሰጡ በርካታ የባህል መድኃኒት እንዳሉ ገልጸው፤መድኃኒቶቹ ይዘታቸውን ሳይለቁ ፈዋሽነታቸውንና ደህንነታቸውን በምርምር በማረጋገጥ በጥራት ለኅብረተሰቡ ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ ባለው የምርምር ማዕከል የመድኃኒት ይዘት ያላቸው የእጽዋት ተክሎችን በማጽደቅ ምርምር እየተደረገባቸው መሆኑንም አስረድተዋል።
በተለይም የባህል መድኃኒትን ተከትሎ የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳቶችን አስቀድሞ ለመለየት ምርምር በዋናነት እንደሚከናወን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ሕጋዊ እውቅና ካላቸውና ስኬታማ ከሆኑ የባህል ሕክምናና መድኃኒት አዋቂዎች ጋር እንደሚሰራ ገልጸው፣ይህም ዘርፉን ከማሳደግ ባሻገር የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ እያገዘ ነው ብለዋል።
በተቋማቱ መካከል የተፈጠረውን ቅንጅታዊ አሰራር በሕግና መመሪያ ለመምራትም ከባህል መድኃኒት አዋቂዎችና ማህበራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ወይዘሮ ፍሬ ሕይወት አስታውቀዋል።
በባህል መድሃኒት አዋቂዎች ምርምር የተደረገባቸውና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒትን ለገበያ ለማቅረብና ጥቅም ላይ ለማዋል የባለሃብቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህል ሐኪምና የአገረሰብ ዕውቀት ተመራማሪ አቶ ሐሚድ አብደላ በበኩላቸው ባህላዊ ሕክምናና መድኃኒት ምዕራባውያን ሕክምና ከመጀመራቸው አስቀድሞ የነበረና አሁንም በተግባር ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
ቻይና፣ጃፓን፣ሕንድ፣ጋናና ኮሪያ እንዲሁም የደቡብ አሜሪካ አገሮች የባህል ሕክምናና መድኃኒትን በስፋት ከሚጠቀሙ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በኢትዮጵያ 85 በመቶ ያክል ዜጎች ኑሮአቸውና የጤና አጠባበቃቸው በባህላዊ ሕክምናና መድኃኒት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።
ይህም ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ስብጥር፤በእምቅ የአገረሰብ እውቀት ክምችትና ተያያዥ ጠቀሜታ ባላቸው መድኃኒታዊ እጽዋት ብዛት በዓለም ከታወቁ አገሮች መካከል በመሆኗ ነው ይላሉ።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ50 ሺህ ለመድኃኒትነት የሚውሉ እጽዋት እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ ያሉት ተመራማሪው፤ ከነዚህም 6 ሺህ ያህሉ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ከመካከላቸው አንድ ሺህዎቹ ለመድኃኒትነት የሚውሉ የእጽዋት ዓይነቶች ሲሆኑ፤ 240ዎቹ አገር በቀል መሆናቸው ተመራማሪው ያስረዳሉ።
በተለይም ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ አንጻር በአገሪቱ የባህል ሕክምናው እየተሰራበት አለመሆኑን አመልክተው፤ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያገኘች አይደለም ብለዋል።
መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በማሳደግ ዘርፉን እንዲያግዝና እንዲደግፍ ተመራማሪው ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገሮች ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች በባህል መድኃኒት እጽዋት ምርትና ገበያ ላይ መሰማራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።