ቀጥታ፡

የውሃ ሙሌቱ የኢትዮጵያን ታላቅነት ዳግም ያረጋገጠና የህዝቡን ተስፋ ያለመለመ ነው-- ምሁራን

ደሴ /ዲላ/ ነገሌ ሐምሌ 18/2012 ( ኢዜአ ) የህዳሴው ግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ የኢትዮጵያዊያን ታላቅነት ያረጋገጠና የህዝቡን ተስፋ ያለመለመ መሆኑን በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ምሁራን ገለጹ።

በሌላ በኩል የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ  ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በጌዴኦ  እና ጉጂ ዞኖች  ነዋሪዎች ተናገሩ። 

በወሎ ዩኒቨርሲቲ  የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት፤ በተስፋና በጉጉት የሚጠበቅ   ነው፡፡

ግድቡ ለፍፃሜ እንዳይደርስ ከጠላት ጋር በመወገን ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ግድቡ ተሸጧል እያሉ ህዝብን ለማሳሳት መሞከር ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።

የውሃ ሙሌቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ መጠናቀቁ ህብረተሰቡ  በግድቡ ላይ ያለውን እምነትና ተስፋ ከፍ እንዲል ማድረጉን  ገልጸዋል፡፡

መንግስት ያደረገው ምክንያታዊና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ድርድርም ፍሬ ማፍራቱን አመልክተው ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ድርድሮችም ምክክርና ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ማንንም ሳትጎዳ እኩል እንጠቀም በማለቷ ልትደገፍ እንጂ ልትነቀፍ እንደማይገባ ጠቁመው፤ አባይን መገደብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ኩራትና ግዴታ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሌላው የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር  ደጀን የማነ በበኩላቸው ሳይታሰብ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት መጠናቀቁ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ብስራትና ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን እምነትና ተስፋ ከፍ ከማድረጉም ባለፈ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

መንግስት ከህብረተሰቡና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ በእቅዱ መሰረት መጓዙ የሚደነቅና የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት፣ ምሁራን፣ ዲያስፖራውና ሌላውም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እውነቱን ለአለም ለማስረዳት ያደረገው ጥረትና ዲፕሎማሲው ፍሬ አፍርቶ የግብጽን ሴራ ማክሸፉ ለዚህ ድል አብቅቷል ብለዋል፡፡

ግብፅና ሱዳንም ኢትዮጰያ የያዘችውን ምክንያታዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተረድተው መደገፍና መተባበር እንዲችሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል  የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሊት በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውንና ግንባታው እስኪጠናቀቅ  ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በጌዴኦ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች  ተናገሩ።

ከነዋሪዎቹ  ወጣት ወንድምአገኝ ኃይሌ እንዳለው ከዚህ ቀደም የቦንድ ግዥን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲደግፍ ቆይቷል።

ይህን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ መያዙ ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረታችን  ማፍራቱን ማሳያ ነው  ያሉት ደግሞ  ወይዘሮ ካሰች ደንበል ናቸው።

ይህም ትልቅ ስኬት ለህዳሴው ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት 8100 ዕጣ በመሳተፍ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙና በቀጣይም የቦንድ ግዥን ጨምሮ በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብሮች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

አቶ እንዳሻው መለሰ በበኩላቸው የለውጡ አመራር ግድቡን ከውድቀት ታድጎ ለዚህ ስኬት ማብቃት የለውጡ ጉዞ አስተማማኝና ትክክለኛውን መስመር እንደያዘ ያሳያል ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የተቀዛቀዘው የህዝብ ድጋፍ እንዲነቃቃ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን የተናገሩት  የጌዴኦ ዞን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የህዝብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ተወካይ አቶ አብርሃም ደመቀ ናቸው።

በዞኑ እስካሁን የቦንድ ግዥን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው በቀጣይም ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ የቦንድ ሽያጭ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በዞኑ የቶሬ ከተማ ነዋሪ መምህር መሐመድ ገመቹ  በሰጡት አስተያየት በቀድሞ አመራሮች ግድቡ እንደተሸጠ አስመስለው ሲያስወሩ በነበረው ሁኔታ ተጠራጥረው መቆየታቸውን ገልጸዋል። 

አሁን  የመጀመሪያ ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱ በስኬት መጠናቀቁን ሲሰሙ ያልጠበቁትና ያላሰቡት በመሆኑ ለማመን ተቸግረው እንደነበር አውስተዋል፡፡

በዚህም በመበረታታት ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ጭምር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡ 

አቶ ሽፈራው መኮንን በበኩላቸው የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነትን ተስፋ የሚያስቆርጥ፤ ኢትዮጵያዊያንን ደግሞ ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት   በሁለት ዙር በ8 ሺህ ብር የገዙትን ቦንድ በእጥፍ በማሳደግ ግድቡ እስኪጠናቀቅ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።፡፡ 

ግድቡ ብሄር ብሄረሰቦች ተባብረን ከሰራን ያሰብነውን ሁሉ የመፈጸምና የመስራት አቅም እንዳለን በተግባር ያየሁበት ነው ያሉት አቶ ወገኔ ተሹ በቀጣይም ቦንድ በመግዛት እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም