የኢትዮጵያ አቋም ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግን የተከተለ ስለመሆኑ ለዓለም እናሳውቃለን -- አምባሳደር ተሾመ ቶጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አቋም ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግን የተከተለ ስለመሆኑ ለዓለም እናሳውቃለን -- አምባሳደር ተሾመ ቶጋ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18/2012 ( ኢዜአ) አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ስለ ዓባይ ወንዝ የያዘችው አቋም ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግጋትን የተከተለ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያሳውቁ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና በኤዥያና ኦሽኒያ የሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የሕዳሴውን ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በዌብናር ውይይቱ ማጠቃለያም የአምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን የጋራ አቋም ያቀረቡት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ውይይቶች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላሉ ብለዋል።
የመጀመሪያ ዓመት የግድቡ የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቁ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ሌሎች ተጨማሪ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደምትችል ማሳያም ነው።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አንገታቸውን ቀና አድርገው በድፍረት መናገር የሚችሉበት ፕሮጀክት ስለመሆኑም መስክረዋል።
ግድቡ 'በአንድነትና በትብብር መስራት አስተምሮናል' ያሉት አምባሳደር ተሾመ 'በእውቀትና በገንዘብ የምናደርገው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረውም ያግዛል' ብለዋል።
"በውጭ ያለን ኢትዮጵያዊያን በማንኛውም ቦታ የግብፅን የሃሰት ትርክትና ፕሮፓጋንዳ በተደራጀ መንገድ ለዓለም ሕዝብ እናስገነዝባለን" ሲሉም ተናግረዋል።
"እኛ ለግድባችን፣ እኛ ለአገራችን" በሚል የተጀመረውን ዓለም አቀፍ ንቅናቄ በመደገፍ ኢትዮጵያ ለሃቅ መቆሟን እናስመሰክራለን" ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን መካከል የሚደረገውን ውስብስብ ድርድር በድል እየተወጡ የሚገኙ ተደራዳሪዎችም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል አምባሳደር ተሾመ ቶጋ።
ተደራዳሪዎች ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለጋራ ተጠቃሚነት የምታደርገው ጥረት ማሳያ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
የኤዥያ አህጉር በርካታ የዓለም ሕዝብ የሚገኝበትና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ተሞክሮ የሚሆኑ ልምዶች የሚገኙበት በመሆኑ መልካም ግንኙነት እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል።
የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ጠንካራ የፍትህ ፍላጎትና እምነት ማስረዳት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው ድርድር በእውቀት የተመላ እልህ አስጨራሽ ድርድር እስካሁን በአሸናፊነት እንድንጓዝ ረድቶናል ነው ያሉት።
በመጀመሪያው ዓመት የውሃ ሙሌት የተፋሰሱ አገራት ከፍተኛ የሆነ ክፋት ምቀኝነትና ትንኮሳ፤ ኮቪድ-19 እንዲሁም የበረሃ አንበጣ ፈተናዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
"አሁንም ፈተናዎች ይጠብቁናል" ያሉት ሚኒስትሩ በተለይ ስምምነት ያልተደረሰባቸው የተራዘመ የድርቅ ዓመታት በየቀኑ የሚለቀቀው የውሃ መጠንና ሌሎች ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ግድቡ እየተገነባ የውሃ ሙሌቱ ይቀጥላል፤ በሚቀጥለው ዓመትም ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ቀሪዎቹ 11 ተርባይኖች ደግሞ እስከ 2015 ይጠናቀቃሉ እንደ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጻ።