የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የአባይ ወንዝ ባለቤትነታችን በዓለም ሁሉ ታውቆና ጸንቶ እንዲኖር አድርጓል -- አቡነ ማቲያስ - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የአባይ ወንዝ ባለቤትነታችን በዓለም ሁሉ ታውቆና ጸንቶ እንዲኖር አድርጓል -- አቡነ ማቲያስ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18/2012 ( ኢዜአ) ''የህልውናችንና የማንነታችን ልዩ ጸጋ የሆነው የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በድል መጠናቀቃችን የአባይ ወንዝ ባለቤትነታችንን በዓለም ሁሉ ታውቆና ጸንቶ እንዲኖር አድርገናል'' ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ገለጹ፡፡
ፓትርያርኩ የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ፓትርያርኩ በመግለጫቸው የሰው ልጅ በስነ ፍጥረት ራሱን እየጠቀመ የፈጣሪውን ክብር በማድነቅና እያመሰገነ እንዲኖር ስልጣን ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያውያን የታሪክና የተፈጥሮ ስጦታቸው በሆነው በአባይ ወንዝ ለረጅም ጊዜያት ሳይጠቀሙበት መቆታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ የኢትዮጵያውያን ሃብት የሆነው ወንዝ ላይ የሚሰራው ግድብ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ግንባታው ተጀምሮ አሁን የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቤተ-ክርስቲያን ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን የገለጹት ፓትርያርኩ፣ ይህን ድጋፍ ለወደፊትም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የግድቡን ግንባታ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱ አካላት የኢትዮጵያ ባለውለታ በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ያለ አንዳች መከፋፈል አብረው መስራት ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያም በብሔር፤ በቋንቋና በሃይማኖት መከፋፈል ሊኖር አይገባም ያሉት አቡነ ማቲያስ፤ ኢትዮጵያ የምንተዛዘንባት፣ የምንተሳሰብባትና የምንፈቃቀርባት አገር እንድትሆን ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣም አስገንዝበዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ለሕዝብ መበሰሩ ይታወሳል፡፡