የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ የዘርፉን ከባቢ ሁኔታ እያሻሻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ የዘርፉን ከባቢ ሁኔታ እያሻሻለ ነው
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 18/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ የዘርፉን ከባቢ ሁኔታ እያሻሻለ መሆኑን ዥንዋ አስነበበ።
መንግሥት ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል የቪዛ ፖሊሲን በማላላት ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ አንዱ አካል ሲሆን ፤በዚህም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ዜጎች ኢትዮጵያ ለመግባት የሚያስችላቸውን ሁኔታ አመቻችቷል ሲል ዘግቧል።
ኢትዮጵያን የጎበኙ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 አስከ 2019 በነበረው ጊዜ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ያላለፈ እንደነበር ጠቅሷል።
በተያዘው 2020 የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የጎብኚዎች ቁጥር መቀነሱንም ሪፖርቱ አመላክቷል።
የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉት 80 የበረራ መዳረሻዎች በኮቪድ 19 ወረረሽኝ ምክንያት በማቋረጡ የዓለም አቀፍ ተጓዦች ቁጥር በ35 በመቶ መቀነሱ ጄ ኤል ኤል የተባለውን ሆቴልና መስተንግዶ ግሩፕ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
"ወረርሽኙን ተከትሎ ያለው የቱሪሰት ፍሰት ቢቀንስም አገሪቱ በዘርፉ ያላት እምቅ አቅም ከፍተኛ ተስፋ ያለው ነው ።
በዩኔስኮ የተመዘገቡ 9 ቅርሶችን የያዘችው ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ መሣሪያ አድርጋ እየተመለከተችው ነው።
በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግም መንግሥት የራሱን ጥረት እያደረገ ነው" ብሏል።
ዓለም አቀፉ የሪል ስቴት ኢንቨስትመንትና አማካሪ ተቋም በኢትዮጵያ ያለውን የሆቴል ኢንዱስትሪ አስመልክቶ ባወጣው ምልከታ "በአገሪቱ ያለው አዎንታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና እየጨመረ የመጣው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለሆቴል ዘርፉ መጨመር አወንታዊ ሚና አለው" ሲል ይገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኮርፖሬት ተቋማት ፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዲፕሎማቲክ ተቋማት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላይ የማድረግ ፍላጎታቸው በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት እየጨመረ ይመጣል ብሏል ሪፖርቱ።
በኢትዮጵያ 21 ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውሶ፤ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ 4 ሺህ 300 አልጋዎች እንደሚኖራቸው አመልክቷል።
በአገሪቱ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ሆቴሎችንና ሎጆችን በመገንባት የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን መሳብ ይገባዋል ሲልም ሪፖርቱ አስገንዝቧል።