ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የፍትህ ጥያቄ ነው -- ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ ሀምሌ 18/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች አገሪቷ በዓባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የፍትህ ጥያቄ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት እንዳለባቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።

ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ የምታንፀባርቀው አቋም በቅኝ ግዛት ያልተያዘችን አገር ቅኝ ግዛትን እንድትቀበል ማስገደድ መሆኑን መረዳት ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በኤዥያና ኦሺኒያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ባለሙያዎች ጋር የዌብናር ኮንፍረንስ አካሂደዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባቸው ፕሮጀክቶች የተፋሰሱን አገራት ጥቅም በማይጎዳ መንገድ ነው።

ከተፋሰሱ አገራት ጋር የምታደርገው ድርድር ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግጋትን የተከተለ ብቻ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የምታደርገው ድርድር ፍትሃዊና ምክንያታዊ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ከመሻት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ የያዘችው አቋም የፍትህ ጥያቄ መሆኑን ማሳወቅ አለባቸው ነው ያሉት።

ኢትዮጵያዊያን በትምህርት ቤቶች፣ በምርምር ተቋማትም ሆነ በየተሰማሩባቸው መስኮች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር አለባቸው ብለዋል ሚኒስትር ገዱ።

ኢትዮጵያዊያን የግብፅን ፕሮፓጋንዳና የፈጠራ ትርክት ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ይገባቸዋልም ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በዜጎች መካከል ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረ ፕሮጀክት ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የውሃ ሕግ መሰረት በተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ ግድቧን ትገነባለች እንጂ የግብፅና የሱዳንን ይሁንታ አትጠብቅም ብለዋል።

ዓባይ የኢትዮጵያ ወንዝ ሆኖ ሳለ ከግብፅ ፈቃድ የምትጠይቅበት ምክንያት የለም፤ ግብፅ ብቸኛዋ አዛዥ የምትሆንበት ጊዜ አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል።

በዓባይ ወንዝ ላይ የሚደረገው ድርድር በአንድ ቀን ማለቅ የሚችል መሆኑን የገለጹት አቶ ገዱ ግብፅ አቋሟን ቀይራ 'ወንዙ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብት ነው' ካላለች "ትግሉ ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም