"ግብፅና ሱዳን የዓባይ ተፋሰስን የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንደማይደግፉት መናገራቸው የማይጠበቅ መልስ ነበር" ዶክተር ይልማ ስለሺ - ኢዜአ አማርኛ
"ግብፅና ሱዳን የዓባይ ተፋሰስን የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንደማይደግፉት መናገራቸው የማይጠበቅ መልስ ነበር" ዶክተር ይልማ ስለሺ
አዲስ አበባ ሀምሌ 18/2012 የአካባቢ ጥበቃ ስራ በመስራት የሕዳሴውን ግድብ ዕድሜ የማራዘም ዕድሉ "በእጃችን ላይ ያለ የውዴታ ግዴታ" እንደሆነ ተገለጸ።
የሕዳሴው ግድብ ተደራዳሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ መሃንዲስ ዶክተር ይልማ ስለሺ "ግብፅና ሱዳን የዓባይ ተፋሰስን የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንደማይደግፉት መናገራቸው የማይጠበቅ መልስ ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።
የውሃ መሃንዲሱ ዶክተር ይልማ ስለሺ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አደርገዋል።
ዶክተር ይልማ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ በነበረው የኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ድርድር ላይ የቆዩ የውሃ መሃንዲስ ሲሆኑ "ከድርድሩ የተማርነው በራስ መተማመንና ፀንቶ መቆምን ነው" ይላሉ።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ኢትዮጵያዊያን በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የመጠቀም መብት ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጡበት መሆኑን ገልጸው ይህ ግን የመጨረሻ ግብ ሊሆን አይገባም ሲሉ አክለዋል።
በተለይ በአረንጓዴ ልማቱ ዘርፍ ሰፊ ርብርብ በማድረግና ጠንክሮ በመስራት ረገድ ኢትዮጵያዊያን ማንንም ሊጠብቁ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
ዶክተር ይልማ የታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገራት በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተጠይቀው ምላሽ እንዲያውም አረንጓዴ ልማት ከተሰራ የሚመጣውን ደለል ስለሚያስቀር ካሳ እንጠይቃል የሚል ያልተጠበቀ ምላሽ መስጠታቸውንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይህን በመገንዘብ የአረንጓዴ ልማቱን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ በሚያስችል መንገድ ማስቀጠል እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሚተከሉት ችግኞች ለእንጨት ኢንዱስትሪ፣ ለግብርና ምርትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያገለግሉ ከሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሊገጥሟቸው የሚችሉ በርካታ ችግሮችን መግታት ይችላሉም ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ሊመጣ የሚችለውን ደለል የማስቀረት ስራ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የሕዳሴው ግድብ እስከ መቶ ዓመት ያለ ምንም የደለል አፈር ጫና በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት፤ ከዚያ በኋላ ግን አቅሙ እየቀነሰም ቢሆን ለ150 ዓመታት እንዲያገለግል ተደርጎ መገንባቱንም ዶክተር ይልማ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ግድቡ ይኖረዋል ተብሎ የታሰበውን የ250 ዓመት አገልግሎት የአካባቢ ጥበቃ ልማቱን በማጠናከር ለበርካታ ዓመታት በሙሉ አቅሙ ማራዘም ይቻላል ነው ያሉት።