የቅርሶች አስተዳደር ሥርዓትን ዓዋጅ ማሻሻያና ክለሳ እየተካሄደ መሆኑን ባለሥስልጣኑ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የቅርሶች አስተዳደር ሥርዓትን ዓዋጅ ማሻሻያና ክለሳ እየተካሄደ መሆኑን ባለሥስልጣኑ ገለጸ
አዲስ አበባ ሀምሌ 18/2012 በኢትዮጵያ የቅርሶች አስተዳደር ሥርዓትን ዓዋጅ ማሻሻያና ክለሳ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
በአገሪቱ የሚገኙ ቅርሶች በ1992 በፀደቀው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ እንዲሁም በ2006 ቅርሶችን በብሔራዊና በክልል ደረጃ በሚመድቡት ዓዋጆች ሲተዳደር መቆየቱ ይታወቃል።
ይህም በተለይ ቅርሶች በታሪክ ምስክርነታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ሳይንሳዊ ምዝገባና ቁጥጥር ማድረግና ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች መከላከል የሚሉት ተግባራት ይገኝበታል።
ከቅርሶች የሚገኙ ጥቅሞች ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት እገዛ ማድረግ፤ ቅርሶችን ማግኘትና ማጥናት እንዲሁም መቆጣጠር የቅርሶች መረጃ መሰብሰብና መለየት ለባለስልጣኑ ከተሰጠው ኃላፊነት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ይሁንና አገሪቱ ካላት የቅርሶች ብዛት አኳያ ማስተዳደሩ በመንግሥት አካል ብቻ ለማከናወን ፈታኝ እንደሆነበት ባለስልጣኑ ይገልጻል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ እስካሁን የነበረው የቅርስ አስተዳደር ሥርዓት ወጥ ያልሆነና ግልጽነት የሚጎድለው ነበር።
ይህም ዓዋጁ በተለይ በአብዛኛው ቅርስ የመመዝገብ፣ የመንከባከብ፣ እድሳትና ጥገና የማድረግና ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች የመከላከል እንዲሁም የማልማት ሥራዎች የባለስልጣኑ ብቻ የሚያስመስል ነውም ይላሉ።
በመሆኑም ተግባራቱን በአቅም በሙያና በሌሎችም ነገሮች ለማከናወን ሌሎችንም አካላት ተሳትፎ በማካተት ዓዋጁን የማሻሻልና የመከለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ክልሎችን በሚመለከትም ቅርሶችን ከመፈለግ፣ ከማግኘት፣ ከመለየት ጀምሮ እስከ ማልማት ድረስ ያለውን በተከለሰው ዓዋጅ ሥርዓት ባለው መንገድ ሚና እንዲኖራቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።
ዓዋጁ ከጸደቀ በኋላም ቅርሶችን በፌደራል ደረጃ የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማልማት ሥራ የሚከናወን ሲሆን፤ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የየራሳቸውን ቅርሶች እንደሚያስተዳድሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ሆኖም ከአቅማቸው በላይ የሆነ የፋይናንስ፤የሙያና የመሳሰሉት ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ባለስልጣኑ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዓዋጁ የሃይማኖት ተቋማት በስነ ሕንጻና በታሪክ ያሰባሰቧቸውን ቅርሶች ጥገናና ልማት ጨምሮ ማስተዳደርን ግዴታና ኃላፊነት ጭምር እንደሚያደርግም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አመልክተዋል።
ቅርስ የአንድ ሕዝብ የዘመናት የኑሮ እንቅስቃሴ፣ የሥራና የፈጠራ ክንውን መዘክርና ተተኪው ትውልድም የማንነቱ መገለጫ በሆነው ታሪክና ባህል ጥልቅና ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ ሚና እንዳለው ይታወቃል።
በመሆኑም ቅርሶችን መንከባከብና መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ይገባዋል ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።