ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

አሶሳ ሐምሌ 18/ 2012 (ኢዜአ)  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀመረ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳሩ አቶ አሻድሊ ሃሰን በጉባኤው እንደተናገሩት ስልጣን ያጣው ኃይል የህዝቦችን ሠላም በማደፍረስ ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ ነበርንበት የቀውስ አዙሪት ለማስገባት እየጣረ ነው፡፡

ለህዝብ የሚጠቅም የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አጃንዳ የሌላቸው እነኚሁ አካላት ከውስጥ እና ከውጪ ኃይሎች የተሰጣቸውን የብጥብጥ ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲደክሙ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ አንዳንዶቹ በጥፋት ኃይሎች ፕሮፓጋንዳ ተወናብደው በንጹሃን ላይ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ መድረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡

በህዝብ እና በመንግስት የተቀናጀ ጥረት ያሰቡትን ያህል ጉዳት ሳይሳካላቸው  የጥፋት እቅዳቸው በአጭር መቀጨቱን አቶ አሻድሊ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉ የኮሮና ቫይረስ  ወረርሽን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታታቱ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡

በዓመታት የተጓተቱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ቁሳቁስ እና ባለሙያ ለማሟላት የተደረገውን ጥረት ጠቅሰዋል፡፡

ወረዳን ከወረዳና ቀበሌ የሚያገናኝ መንገድ፣ በወረራ የተያዙ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እና የማዕድን ስፍራዎችን ለአልሚ ወጣቶች መተላለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡

በግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ገቢ አሰባሰብ፣ መጠጥ ውሃ ፣ ትምህርት ተቋማት ማስፋፊያ እና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል፡፡

ጉባኤው እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን የክልሉ ምክር ቤት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ዋናው ኦዲት ቢሮ ያለፈው በጀት ዓመት ስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።፡

የክልሉ የ2013 ስራ ዘመን በጀት እንደሚቀርብና  የዳኞች ሹመት እንደሚሰጥ ለጉባኤው የወጣው ፕሮግራም ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም