የግድቡ የውሃ ሙሌት በቀጣይም ታሪክ እንደምንሰራ ያረጋግጥንበት ነው-- ዋና አፈ ጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ የውሃ ሙሌት በቀጣይም ታሪክ እንደምንሰራ ያረጋግጥንበት ነው-- ዋና አፈ ጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ
ባህርዳር ሐምሌ 18/2012 (ኢዜአ) " ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በቀጣይም ታሪክ እንደምንሰራ የረጋግጥንበት ነው” ሲሉ የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ ገለጹ።
ዋና አፈ ጉባኤዋ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት አስመልክተው ለመላው ኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚሁ መልዕክታቸው የህብረታችንና የአንድነታችን ምንጭ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የህዝብና የመንግስት የመናበብ ውጤት ነው ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ከራሱ አካባቢ መንጭቶ የሚፈሰው የአባይ ወንዝ እስካሁን ከጨለማ ኑሮ ያላላቀቀው መሆኑ ለቁጭት ሲዳርገው እንደኖረ አውስተዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የክልሉ ህዝብ ቁጭቱን ለመወጣት በቦንድ ግዥ፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ በማከናወንና በገንዘብ ልገሳ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ህዝቡ የተነቃነቀበትና የሃሳብ አንድነት የያዘበት ጉዳይም አባይ የራሱ ሃብትና የውሃው ባለቤት ቢሆንም ራሱ ሳይጠቀም ሌሎች ሀገራት በብቸኝነት ሲጠቀሙበት መኖሩን ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር አባይን መገደብ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በላይ ማድረግ የሚችልና ታሪክ የሚሰራ መሆኑን በግድቡ ውሃ ሙሌት ተረጋግጧል ብለዋል።
ዋና አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት መንግስትና ህዝብ ባደረጉት የጋራ ጥረት የታላቁ ህዳሴ ግድብ በመገንባት የመጀመሪያው ምዕራፍ የውሃ ሙሌት መካሄዱ ለብልጽግና ጉዞ መሳካት ጉልህ ሚና አለው።
"የህዳሴው ግድብ ብልጽግናችን እስኪያረጋግጥ ድረስ የህዝባችን ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ግድቡ እንዳይሞላ የጠነሰሱት ሴራ ያከሸፈ ታሪክ ዳግም መሰራቱን ገልጸው "በቀጣይም ታሪክ እንደምንሰራ የረጋግጥንበት ነው " ሲሉ አስታውቀዋል።
በቀጣይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀሪ ስራዎች ላይ በተቋም ደረጃም ሆነ በህዝባዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዛሬም እንደትናንቱ ይሰራል ብለዋል።